ሶከር ሜዲካል | የጉልበት ጉዳት በእግርኳስ

እግርኳስ የንክኪ ስፖርት እንደመሆኑ በርካታ ጉዳቶች ይታዩበታል። አንደ ጡንቻ መሸማቀቅ ያሉ ቀለል ያሉ ጉዳቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ የሚገኝላቸው እና እምብዛም ለክፉ የማይዳርጉ ሲሆኑ እንደ ጉልበት እና ቁርጭምጭሚት ያሉት ጉዳቶች ደግሞ ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ የሚያርቁ እና ለተለያዩ ውስብስብ አደጋዎች የሚያጋልጡ ናቸው።

የፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቸች ማህበር – ፊፍ ፕሮ – ባከናወነው ጥናት መሰረት እድሜያቸው ከ40 በላይ ከሆኑ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾች ውስጥ በአማካይ ከሶስቱ አንዱ በጉልበቱ ላይ የሚገኘው ልስልስ አጥንት (Cartillage) ጉዳት ያጋጥመዋል። በተያያዘም ከ900 በላይ በሆኑ እግርኳስን ተጫውተው ባሳለፉ ሰዎች ላይ በተሰራ ጥናት መሰረት 35% የሚሆኑት ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው የቀድሞ ተጫዋቾች በመገጣጠሚያ አካላት ላይ ያለ እና የመገጣጠሚያውን ፍትጊያ የሚቀንስ ልስልስ አጥንት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ምክኒያት የሚከሰት ኦስቴኦአርትራይተስ (Osteoarthritis) የተባለ በሽታ ተጠቂ እንደሆኑ ተረጋግጧል። የእግር ኳስ ተጫዋቾች እንደዚህ ላለው በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከሌላው ሰው 2.5 እጥፍ እንደሆነም ይገመታል።

ጉልበት ፓቴላ (Patella) ከተሰኘ አጥንትና ከተለያዩ ጅማቶች የተዋቀረ መገጣጠሚያ ነው። ከላይ ፌሙር (Femur)፤ ከታች ደግሞ ቲቢያ (Tibia) እና ፊቡላ (Fibula) በተባሉ አጥንቶች ይዋሰናል። በዙሪያውም ምንም አይነት ስብ የለም። ጉልበት ሰውነታችን ለሚያከናውናቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ግልጋሎትን ይሰጣል። የጉልበት መገጣጠሚያ እንደ ፈለግን እግራችንን በማጠፍ እና በመዘርጋት ለመራመድም ሆነ ለመሮጥ ይረዳናል። ተጫዋቾችም ኳስን እንደ መምታት ባሉ እንቅስቃሴዎች ይጠቀሙበታል።

የጉልበት ጉዳት ሲባል በዙሪያው የሚገኙ አጥንቶች፣ ጅማቶች እና ካርቲሌጆች ላይ የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን አቅፎ የያዘ ሲሆን በእግርኳሱ ከሚከሰቱ እና ለማገገም ረጅም ጊዜ ከመውሰድ አልፈው ተጫዋቾች ያለዕድሜያቸው ከእግርኳሱ እንዲገለሉ ከሚያደርጉ ከባድ ጉዳቶች ውስጥ አንዱ ነው።
በ1994ቱ የዓለም ዋንጫ ለስዊድን ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ፖንተስ ካማርክ “በተደጋጋሚ የጉልበት ጉዳት ውስጥ ሲጫወቱ የነበሩ እና በአሁኑ ሰዓት ለመራመድ እንኳን ተቸግረው ለአካል ጉዳት የተዳረጉ የማውቃቸው በእድሜ የገፉ የቀድሞ ተጫዋቾች አሉ፤” ሲል ስለ ጉልበት ጉዳት ይናገራል። በ2002 የዓለም ዋንጫ የስዊድን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የመካተት ጥያቄ ቢቀርብለትም ከጉዳት ስሜት ጋር ላለመጫወት ሲል ከቡድኑ ራሱን ያገለለው ካማርክ “ሀኪሜ በጉልበቴ ላይ የሚገኘው አጥንት እጅጉን መሳሳቱን ተከትሎ ኳስ እንዳቆም መከረኝ፤” በማለት በ32 አመቱ ኳስን እንዲያቆም ስላስገደደው የCruciate ጅማት ጉዳት ያስታውሳል።

የተለያዩ የጉልበት ጉዳቶች ሲደጋገሙ እንደ Osteoarthritis ላሉ የከፉ በሽታዎች ያጋልጣሉ። ለዚህም ነው የክለብ የህክምና ባለሙያዎች ለጉልበት ጉዳቶች አጽንኦት ሰጥተው መከታተል ያለባቸው።

የጉልበት ጉዳት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የህመም ስሜት ያመጣል፤ ለዚህም ሲባል ተጫዋቾች የቀዶ ህክምናን እንደ መፍትሄ ያደርጋሉ። በጉልበት ላይ የሚደረገው ይህ ቀዶ ጥገና አመትና ከዛም በላይ ከሜዳ ሊያርቅ ይችላል። ህክምናው ጉዳቱ ስር ሳይሰድ በፍጥነት የሚሰራ ከሆነ ውጤታማነቱ ላቅ ያለ ከመሆኑም ባሻገር ለማገገሚያ የሚያስፈልገው ጊዜ አነስ ያለ ይሆናል።

ለስዊድኑ ክለብ ማልሞ ተጫውቶ ያሳለፈው ራስመስ ቤንግስተን ከጉልበት ህመም ጋር እየተሰቃየ ያለምንም እርዳታ ለረጅም ጊዜ መጫወቱን ይናገራል። ጊዜያዊ የህክምና እርዳታ ማግኘት አለመቻሉም በወቅቱ ወጣት ስለነበር እና ብቃቱን ለማሳየት ከነበረው ጉጉት የመነጨ መሆኑን ይመሰክራል።

ይህ በብዙ ተጫዋቾች የሚስተዋል አመለካከት ነው። እግርኳስ የገቢ ምንጫቸው መሆኑን ተከትሎ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ የሚርቁ እና ህመማቸውን አውጥተው ሲናገሩ የማገኘው ጥቅም ይጎድላል የሚል ፍራቻ ስላለባቸው አፋጣኝ የህክምና እርዳታን ለማግኘት ያመነታሉ። በመሆኑም በቀላሉ ሊቆጣጠሩት ይችሉት የነበረው ችግር ብዙ መዘዝን ይዞ ይመጣል።

ስቴቨን ሌንሃርት የተሰኘው ተጫዋች ለፊፋ ፕሮ ሲናገር “ተጫዋቾች በተቻለ መጠን ሰውነታቸውን እና ያለበትን ሁኔታ ማዳመጥ መቻል አለባቸው። ህመም እየተሰማቸው የመጫወት ግዴታ ውስጥ መግባት የለባቸውም፤” በማለት በዚህ አሳሳቢ ጉዳት ዙሪያ ለስፖርተኞች ምክሩን ለግሷል።

እንደዚህ ያለው ችግር ለህክምና በቂ ትኩረት በማይሰጠው እና በቂ ባለሙያ በሌለበት እግር ኳሳችን ላይ መስተዋሉ የማይቀር ነው። ጉዳት ያጋጠመው ተጫዋች ያለ በቂ መፍትሄ ብዙ እንግልት እንደሚያይም ግልፅ ነው። ከሁሉም በላይ ዋናው ነገር ጤና ነውና ተጫዋቾች በጊዜ ስሜቶቻቸውን ሊያዳምጡ፣ ለክለቦች ሊያሳዉቁ እና በቂ የሆነ የህክምና አገልግሎት ሊያገኙ ይገባል። ይህ የማይሆን ከሆነ የእግር ኳስ ህይወታቸውን ከማሳጠሩም ባሻገር ከዛም በኋላ በሚኖራቸው ኑሮ ላይ ተፅዕኖን ያሳድራል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *