ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር ወደ መሪው የተጠጋበትን ድል አስመዝግቧል

የ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7 ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ሲደረጉ ጅማ ላይ መቐለ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር 1-0 በማሸነፍ ወደ መሪው የተጠጋበትን ውጤት አስመዝግቧል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ በተቀመጡ ክለቦች መሃከል የተደረገ እንደመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው ከተጠበቁ የሳምንቱ ጨዋታዎች አንዱ ነበር። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በከተማው የሚገኘው ፋኖ ስፖርት ለጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄ የክለቡ የወሩ ኮከብ በማለት ሽልማት አበርክቶለታል፡፡

የመጀመርያውን አጋማሽ የጀመሩት ጅማ አባ ጅፋሮች ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ከመሃል የተነሳውን ኳስ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ መቐለ የግብ ክልል በመድረስ በኦኪኪ አማካኝነት አስደንጋጭ ሙከራ አድርገዋል። ከዚህ ሙከራ በኋላ በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች አባ ጅፋሮች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም ለግብ የቀረበ ዕድል ያገኙት ግን መቐለዎች ነበሩ። በ7ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር አማኑኤል ገ/ሚካኤል  ያሻገረውን ኳስ ፉሴይኒ ኑሁ ሞክሮ በዳንኤል ኦጂ ጥረት ወደ ግብነት ሳይቀየር ቀርቷል።
መቐለ ከተማዎች ምንም እንኳን የጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በጋቶች ፖኖም አማካኝነት በተደጋጋሚ ከርቀት አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል። ጋቶች በተለይም በ16ኛው ደቂቃ በግምት ከግቡ ከ25 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣበት ሙከራ በመቐለዎች በኩል ተጠቃሽ ነበር፡፡

በጅማ አባጅፋር በኩል ከቀኝና ከግራ መስመር የሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች እንደ ወትሮ ውጤታማ አልነበሩም። በዚህም የተነሳ አሰልጣኝ ገብረመድህን ተጫዋቾቻቸው ኳስን መስርተው እንዲጫወቱ መመሪያ ሲሰጡ ቢታዩም አንዳንድ ተጫዋቾች ይህንን መተግበር ባለመቻላቸው ደስተኛ እንዳልነበሩ ታይቷል። በአባ ጅፋሮች በኩል ከቆሙ ኳሶች ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በ45ኛው ደቂቃ ኦኪኪ ከግራ መስመር የመቐለ ተከላካዮች አታሎ ከፊሊፕ ኦቮኖ ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም በግብ ጠባቂው ድንቅ ጥረት ግብ ሳይሆን የቀረው ኳስ ጅማ አባ ጅፋሮች በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉት ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። በዚህ ሁኔታም የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለጊዜ ያለግብ ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ የመጀመሪያውን የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት መቐለ ከተማዎች ሲሆኑ በ46ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ያሻገረውን ኳስ ፉሴይኒ ኑሁ አግኝቶት ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ ግልፅ  የግብ ዕድል ቢፈጠርለትም ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ሰዶታል። ከሙከራው በኃላ አባ ጅፋሮች ከመጀመርያው አጋማሽ ረጃጅም ኳሶች ይልቅ በፍጥነት በአንድ ሁለት ቅብብል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል። በ51ኛው ደቂቃም ከጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል በኋላ ሄኖክ አዱኛ ኳስን ከቀኝ መስመር ሲያሻግር ኦኪኪ አፎላቢ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ጅማ አባ ጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል።

መቐለ ከተማዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ባደረጉት ጥረት በ65ኛው ደቂቃ ጋቾች ፓኖም ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ በድጋሚ ለፉሴይኒ ኑሁ ቢደርሰውም ሊጠቀምበት አልቻለም። በቀሪ ደቂቃዎች በአባ ጅፋር በኩል ኦኪኪ አፎላቢ እና ሳምሶን ቆልቻ ያደረጓቸውን አሰደንጋጭ የግንባር  ሙከራዎች በዕለቱ ጥሩ በነበረው የመቐለው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ መክሸፋቸው የግብ ልዩነቱ እንዳይሰፋ አድርጓል።

ጨዋታው በጅማ አባ ጅፋር 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለ ከተማ ከነበረበት 4ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ለመውረድ ሲገደድ ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ብሎ ከመሪው ደደቢት ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ማጥበብ ችሏል።

አስተያየቶች

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር

ጥሩ ጨዋታ ነበር። ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር በሁለተኛው አጋማሽ እንደ ተጋጣሚያችን አጨዋወት የታክቲክ ለውጥ አድርገናል፤ ተሳክቶልናልም። ማሸነፍ ችለናል፤ ደስተኛ ነኝ።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ

በጨዋታው ጥሩ ነበሩ፤ ብዙም ውጤታማ ባይሆንም ከኛ በተሻለ ጥሩ ክሮስ ያደርጉ ነበር። ሆኖም ግብ አስቆጥረው መሸነፍ ችለዋል። ምንም ማድረግ አይቻልም፤ ለቀጣይ ጨዋታዎች ተዘጋጅተን እቀርባለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *