ኢትዮጵያ እና ግብፅ በወዳጅነት ጨዋታ ይገናኛሉ

የግብፅ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ጀማል አላም እና ዋና ፀሐፊው ካሪም ሼሃታ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በነሐሴ ወር ከኢትዮጵያ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ እንደተስማሙ ገልፀዋል።

ግብፅ በአስዋን ከተማ ያስገነባችው አዲስ ስታዲየም በሚመረቅበት ዕለት ከኢትዮጵያ ጋር ጨዋታ ለማድረግ በማቀድ ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ጥያቄውን እንደተቀበለው ነው የተነገረው።

ሁለቱ ሃገራት ሞሮኮ ለምታዘጋጀው የ2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቋቸው ሲሆን የወዳጅነት ግጥሚያውም በጳጉሜ እና መስከረም ለሚደረጉት የማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት የሚረዳቸው ይሆናል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞዋን አልጄሪያ እና ማሊን አዲስ አበባ ላይ በመግጠም የምትጀምር ሲሆን ግብፅ ደግሞ ከሴኔጋል እና ቱኒዚያ ከባድ ፈተና ይጠብቃታል።

ግብፅ ከሃገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾቿ ነሐሴ 14 ካይሮ እንዲሰበሰቡ ጥሪ ያደረገች ሲሆን ከነሐሴ 19 ጀምሮ ደግሞ ወደ አስዋን ከተማ በመጓዝ ልምምድ የሚጀምሩ ይሆናል። ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገው ጨዋታም በዚያ ሳምንት መጨረሻ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ እና ግብፅ በዋናው ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሲገናኙ ከ12 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በኦገስት ወር 2002 (እ.ኤ.አ) በወዳጅነት ጨዋታ ነው፡፡ ፈርኦኖቹ ጨዋታውን በ4-1 ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *