” በውጤቱ በጣም ተደስቻለሁ ” ሙሉዓለም መስፍን

በ21ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ባገናኘው ወሳኝ ጨዋታ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሲያሸንፍ በመጨረሻው ደቂቃ ወሳኙን ጎል ያስቆጠረው አማካዩ ሙሉዓለም መስፍን ነው። ዘነድሮ ቡድኑን የተቀላቀለውና የመጀመርያ ጎሉን በዛሬው እለት ያስቆጠረው ሙሉዓለም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በጣም ውጥረት የተሞላበት እና በታክቲክ የታጠረ በመሆኑ በእኛም በእነሱም በኩል ምንም አይነት ነፃ ቦታ አልተገኘም። የተጠበቀውን ያህል ሳቢ ጨዋታ ነበር ባይባልም ያገኘነውን አጋጣሚ ተጠቅመን አሸንፈን ወጥተናል። ይህ ደግሞ ለቡድናችን ወሳኝ ሦስት ነጥብ ያገኘበት በመሆኑ በውጤቱ በጣም ተደስቻለሁ። 

ስለ ቡድኑ እና የግል አቋሙ 

የአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ጥሩ ነበርን። በፕሪምየር ሊጉም ጅማሮ ላይም ጥሩ ነበርን። በኋላ ላይ የተጫዋች ጉዳት አጋጥሞን ስለነበር ነጥቦችን ጥለናል። የአጥቂ መስመራችን ላይ የጎል አጋጣሚዎችን ያለመጠቀም ችግሮች እና  ጫናዎች ነበሩ። በዚህ የተነሳ ከማሸነፍ ስነ ልቦና ወጥተን ነበር። በኋላ ግን የደጋፊዎች እገዛ ተጨምሮበት ቡድኑ እየተሻሻለ መጥቷል ። በግሌ የእኔ እንቅስቃሴ ቡድኑ ደከም ሲል የቀዘቀዝኩበት አጋጣሚ ነበር።  ነገር ግን ጠንክሬ በመስራት ራሴን አሻሽዬ ለመቅረብ ችያለው። ከዚህ በኋላም ከዚህ በተሻለ ቡድኔን ለማገልገል እሰራለው ።


ስለ አሰልጣኙ

ቡድኑ ወደ አዲስ የአጨዋወት ሽግግር ውስጥ ነው የሚገኘው። በሚፈለገው መንገድ አሁንም መሻሻል የሚቀሩን ነገሮች አሉ። አዲስ በዘንድሮ አመት ቡድኑን የተቀላቀልነው ከነባሮቹ ጋር ለመዋሀድ ተቸግረን የነበረ ቢሆንም አሰልጣኙ ጥሩ ነገሮችን እያሳየን አሁን እየተላመድን ነው። ጥሩ መነቃቃት አለን ፤ እንግዲህ መልካም ነገሮችን በየጨዋታው ለማሳየት እንጥራለን።

በቀጣይ…

አሁን ብዙ የጨዋታ መደራረብ የለብንም። ከአፍሪካ ውድድር ውጭ በመሆናችን ዛሬ ሁላችንም በጨዋታው ላይ ሙሉ አቅማችንን ሰተናል።  በቀጣይ ያለንን አቅም ተጠቅመን ጥሩ ነገር መስራት አለብን። ያለን አንድ ዋንጫ ይሄ ነው። ያለንን አቅም አውጥተን ዋንጫውን እናነሳለን።