ከፍተኛ ሊግ – ለ | ሀላባ መሪነቱን ሲያጠናክር አባ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ ደረጃቸውን አሻሽለዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጨዋታዎች ቅዳሜ ተደርገው ሀላባ ከተማ መሪነቱን ሲያጠናክር ደቡብ ፖሊስ እና ጅማ አባ ቡና ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል አስመዝግበዋል።

ጅማ አባ ቡና 3-0 ቤንች ማጂ ቡና

(በቴዎድሮስ ታደሰ)

ጅማ ስታድየም ላይ ቤንች ማጂ ቡናን ያስተናገደው ጅማ አባቡናን 3-0 በማሸነፍ  ደረጃውን አሻሽሏል። ጨዋታው ሳቢ ያልነበረ ሲሆን ቤንች ማጂዎች ሙሉ ለሙሉ መከላከል እና ጉልበት ላይ ያመዘነ ጨዋታን ተከትለው ለመጫወት ተገደዋል። አባቡናዎች ምንም እንኳን የመጀመርያውን አጋማሽ በተመስገን ደረሰ 34ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል በመምራት ቢያጠናቅቁም በእንቅስቃሴ ረገድ ባልተሳኩ ቅብብሎች እና ያልተደራጀ የጨዋታ እንቅስቃሴ እንዲሁም የቤንች ማጂን የተከላካይ መስመር ማለፍ ሲቸገሩ ተመልክተናል።
ከእረፍት መልስ በይበልጥ በሽኩቻዎች ታጅቦ ቤንች ማጂ ተጫዋቾች እያንዳንዱን የዳኛ ውሳኔ ሲቃወሙ እና አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ሲገቡ ተስተውለዋል። በ50ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ እንደሻው አባቡናን መሪነት ወደ 2-0 መሪነት ከፍ ያደረገች ግብ ካስቆጠረ በኋላ ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር አባቡናዎች ወደግብ ቶሎ ቶሎ በመድረስና የኳስ ቁጥጥር ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ችለዋል። በ68ኛው ደቂቃ ብዙአየሁ እንደሻው ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ መጠለፉን ተከትሎ የመሀል ዳኛው የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት በመቃወም ከዳኛው ጋር ግብግብ የገጠሙት የቤንች ማጂ ተጫዋቾች ጌታሁን ገላዬ እና አበራ አየለ ከሜዳ በቀይ ካርድ እንዲወጡ ተደርጓል። በሁኔታው ጨዋታው ለ10 ደቂቃዎች ተቋርጦ ከቀጠለ በኋላ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ብዙአየሁ አስቆጥሮ አባቡናን 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ያስቻለውን ውጤት አስመዝግቧል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ቤንች ማጂ የቡድን አባላት ሜዳ በመግባት የእለቱ አልቢትሮች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ቢሞክሩም በእለቱ በነበሩበት የፀጥታ አካላት ርብርብ አርቢትሮች ላይ ጉዳት ሳይደርስ የቀረ ሲሆን የግብ ጠባቂው አሰልጣኝ ታፈሰ አጃ ቀይ ካርድ ተመልክቷል። ከሁሉም በላይ አስገራሚው ግብ ጠባቂው አብዱልሃፊዝ መኪ ከዳኛው አልፍ ተርፎ ፀጥታ በማስከበርና ለዳኞች ከለላ ለሰጠው የኮማንድ ፖስት አባል የሆነው የፌዴራል ፖሊስ ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ ነገሮች አቅጣጫዎችን በመቀየር ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ለረጅም ደቂቃዎች በፀጥታ አካላት እና በእለቱ የጨዋታ ኮሚሽነር ዩሀንስ ስለሺ አሸማጋይነት ከቆዩ በኃላ በኮሚሽነሩ ጥረትና የፀጥታ አስከባሪ አካላት ሁኔታውን በማብረዳቸው በህግ ቁጥጥር ስር ሳይውል ቀርቷል፡፡
ሌሎች ጨዋታዎች

(በአምሀ ተስፋዬ)

ሀላባ ላይ በ10:00 ድሬዳዋ ፖሊስን ያስተናገደው ሀላባ ከተማ በ23ኛው ደቂቃ ስንታየሁ መንግስቱ በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል 1-0 አሸንፏል። በዚህም ውጤት መሰረት ሀላባ ከተማ በ31 ነጥቦች የምድብ ለ መሪነትን ማጠናከር ችሏል።
ደቡብ ፖሊስ በሜዳው በግብ መንበሽበሹን ቀጥሎ ከመቂ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ 4-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በ10ኛው ደቂቃ ብሩክ ኤልያስ ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር በ18ኛው ደቂቃ አበባየው ዮሐንስ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሮ ወደ ዕረፍት አምርተዋል። በ53ኛው ደቂቃ ኤሪክ ሙራንዳ በፍፁም ቅጣት ምት 3ኛውን ሲያክል በ82ኛው ደቂቃ አራተኛ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህ ውጤት መሰረት ደቡብ ፖሊስ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል።
ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ሻሸመኔ ከተማን አስተናግዶ በሀቁ ምንይሁን ገዛኸኝ የ5ኛው ደቂቃ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሎል። ነገሌ ላይ ነገሌ ከተማ ቡታጅራ ከተማን 1-0 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ላይ ረፋድ 04:00 ናሽናል ሴሜንት በሳሙኤል ዘሪሁን ጎሎች ወልቂጤ ከተማን 2-1 መርታት ችሏል። በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ የነበረው ዲላ ከተማ ደግሞ ወደ ዱራሜ ተጎዞ ከሀምበሪቾ ጋር ያለጎል አቻ በመለያየት ከደረጃው ለመንሸራተት ተገዷል።