ከፍተኛ ሊግ – ሀ | በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታዎች ባህርዳር እና አአ ከተማ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ ቅዳሜ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀምር መሪው ባህርዳር ከተማ እና ተከታዩ አአ ከተማ አሸንፈዋል። ሽረ እንዳስላሴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 

አክሱም ላይ ሊካሄድ መርሀ ግብር ወጥቶለት ወደ አዲስ አበባ የዞረው የአክሱም ከተማ እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ በምድቡ መሪ ባህርዳር 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ኦሜድላ ሜዳ ላይ በ08:00 በተደረገው በዚህ ጨዋታ ዳግም ሙሉጌታ በክፍት ጨዋታ በ20ኛው እንዲሁም አምበሉ ደረጄ መንግስቱ በፍፁም ቅጣት ምት በ28ኛው ደቂቃ ላይ ለባህርዳር ሲያስቆጥሩ ለአክሱም ከተማ ብቸኛውን ግብ ሽመክት ግርማ በቅጣት ምት  አስቆጥሯል። በዚህም ውጤት መሰረት ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 35 በማድረስ የምድብ ሀ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።
08:00 ላይ በመድን ሜዳ ሱሉልታ ከተማን ያስተናገደው አዲስ አበባ ከተማ 3-1 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል። በትራንስፖርት ችግር ምክንያት በሰዓታቸው ያልተገኙት ሱሉልታ ከተማዋች ፊሽካ ከተነፋ በ20 ደቂቃ ላይ ዘግይተው ቢደርሱም በህጉ መሰረት 30 ደቂቃ ሳይሞላው በመገኘታቸው ጨዋታውን ማድረግ ችለዋል። ብዙም ማራኪ ባልነበረው የሁለቱ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የተጫዋቾች ጉሽሚያ የበዛበት ነበር። የሱሉልታ ከተማው ኤርሚያስ ዳንኤል ከርቀት የመታውና ፍሬው ጌታሁን ያዳነበት በመጀመሪያው 10 ደቂቃ ውስጥ የታየ ብቸኛ ሙከራ ነበር። በቀጣይ 15 ደቂቃዎች የአዲስ አበባ ከተማ የበላይነት የታየበት ሲሆን በ23ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ፍቃዱ አለሙ ከሱሉልታ ተከላካይ ጋር መሬት በመሬት በመሸራተት ወደግብነት ለውጦታል። ግቧም በፍቃዱ አለሙ ተመዝግባለች። ከግቡ መቆጠር ባኃላ በ31ኛው ደቂቃ ሱሉልታዋች ያገኙትን የማዕዘን ምት በሚሻሙበት ወቅት የአዲስ አበባ ግብ ጠባቂ ፍሬው ከሱሉልታ ተጫዋች ጋር በአየር ላይ ተጋጭቶ ከጭንቅላቱ ደም በመፍሰሱ ለጥቂት ደቂቃ የተቋረጠ ሲሆን የሚገኘውን አጋጣሚ ወደፊት በማሻገር የአቻነት ግብ ሲፈልጉ የነበሩት ሱሉልታዋች ቶሎሳ ንጉሴ ከኤርሚያስ የተሰጠውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ሲገባ በተሰራበት ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኤርሚያስ ዳንኤል ወደግብነት ለውጦ አቻ በመሆን የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያው 5 ደቂቃዎች እንዳለማው እና ሙሀጅር የሞከሯቸው አገመጣሚዎች በድጋሚ መሪ ሊሚሆኑባቸው የሚያስችሉ የነበሩ ቢሆንም በሱልልታ ግብ ጠባቂ እና ተከላካይ ጥረት ሳይሳኩ ቀርተዋል። በተቃራኒው ኤርሚያስ ዳንኤል በብቸኝነት በፊት መስመር ላይ  ያሰለፈው ሱሉልታ በርካታ የግብ እድሎችን በአጥቂው አማካኝነት ፈጥሯል። በተለይም በ53ኛው እና 82ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ በመግጨት የሞከራቸው ሙከራዋች የአዲስ አበባው ግብ ጠባቂ የግል ብቃት ታክሎበት ወደግብነት ሳይለወጡ ቀርተዋል። በ55ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ፋሲል   ጌታቸው በግንባሩ በመግጨት አአ ከተማን በድጋሚ መሪ ማድረግ ሲችል በ74ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ ገናናው ረጋሳ ተጨማሪውን አክሎ ጨዋታው በአአ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በውጤቱም አአ ከተማ ነጥቡን 33 አድርሶ ሁለተኛ ደረጃን ከሽረ መረከብ ችሏል።
ቀጥሎ በመድን ሜዳ የተደረገው የኢትዮጵያ መድን እና ሽረ እንዳስላሴ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። የመጀመሪያ ዙር ሲጠናቀቅ ከዋና አሰልጣኙ ደረጀ በላይ ጋር የተለያየው ኢትዮጽያ መድን በቀድሞው የቡድኑ ኮከብ ሀሰን በሽር እየተመራ ወደ ሜዳ ገብቷል። በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ኢትዮጽያ መድኖች በእንቅስቃሴም ሆነ በግብ ሙከራ የተሻሉ ነበሩ። ሀብታሙ መንገሻ በ8ኛው ደቂቃ እና ናይጄሪያዊ አዳም ሳሙኤል በ10ኛው እና በ14ኛው ደቂቃ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችንም አድርገው ነበር። በ17ኛው ደቂቃ አዳም ሳሙኤል ተመትቻለው ብሎ ወድቆ የነበር ቢሆንም የዕለቱ ዳኛ ባለማያታቸው ጨዋታው ቢቀጥልም አዳም ከወደቀበት ተነስቶ ከሽሬ ተከላካይ ጋር በመጋጨቱ የዕለቱ ዳኛ ለአዳም የቀይ ካርድ በመስጠት ከሜዳ እንዲወጣ አድርገዋል። የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው መድኖች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ብልጫ ተወስዶባቸዋል። በዚህም በ22ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር በቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ተከላካዮች በግንባር ገጭተው ቢያውጡትም በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ዘላለም በረከት ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ሽረ እንዳስላሴን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ የሽሬው አጥቂ ልደቱ ለማ በ46ኛው ደቂቃ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ49ኛው ደቂቃ ኳስ የሽረ ግብ ክልል ውስጥ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ ጌታቸው ወደ ግብነት ለውጦት ኢትዮጵያ መድኖች አቻ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር ባኋላ ወደኃላ ያፈገፈጉት መድኖች በመከላከሉ ረገድ ጥንካራ ነበሩ። በ80ኛው ደቂቃ ብሩክ ገብረአብ የመታው ኳስ የግቡን የውስጠኛ ብረት መጥቶት ቢወጣበት ጊዜ አጥቂው ልደቱ ለማ የተመለሰውን ኳስ ሊመታ ሲል ተጎተቶ የነበረ ቢሆንም የእለቱ ዳኛ በዝምታ አልፈውታል። አብዘኛውን ጊዜ በመከላከል የተጠመዱት መድኖች ረጃጅም ኳስ ለታምሩ ባልቻ በመጣል ሁለት ለግብ የደረሰ ሙከራዎችን ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አድኖበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በኦሜድላ ሜዳ 10:00 ላይ ፌዴራል ፖሊስ በሰንጠረዡ አናት ከሚፎካከሩ ቡድኖች አንዱ የሆነው ቡራዩ ከተማን ጋብዞ 1-0 አሸንፏል። የፌዴራልን ወሳኝ የድል ጎል በ24ኛው ደቂቃ ማስቆጠር የቻለው አብዱልከሪም ዘዋን ነው። በያያ ቪሌጅ ኢኮስኮን ከአማራ ውሃ ስራ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በ29ኛው ደቂቃ አማራ ውሃ ስራ በግብ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ከዕረፍት መልስ በ53ኛው ደቂቃ አበበ ታደሰ ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ኮምቦልቻ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ በነቀምት 1-0 በሆነ ውጤት ሲሸነፍ ለገጣፎ ከ ደሴ ከተማ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሰበታ ላይ ሰበታ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ እስከ 20ኛው ደቂቃ ብቻ ከዘለቀ ባኋላ በጣለው ዝናብ ምክንያት ሳይቀጥል ተቋርጦል። ጨዋታው ዛሬ 5:30 ላይ ከቆመበት የሚቀጥል ይሆናል።