​ሪፖርት | የወንድሜነህ አይናለም ድንቅ አጨራረስ ለሲዳማ ቡና ወሳኝ ነጥብ አስገኝቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ድል እየራቀው የመጣው ደደቢትን ይርጋለም ላይ ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በወንድሜነህ አይናለም ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

በሲዳማ ቡና በኩል ደጋፊዎች ህጋዊ የደጋፊ ማህበር እንዲቋቋምላቸው ሰሞኑን ባሰሙት ተቃውሞ ከክለቡ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን ክለቡን የጠንካራ ደጋፊዎች ባለቤት ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ማህበሩን በማቋቋም የዛሬው ጨዋታ ከመካሄዱ በፊት የደጋፊ ማህበሩ  ተመራጮችን ማስተዋወቅ እና በጋራ አብሮ የመስራት መልዕክትን ማስተላለፍ ተችሏል።

ደደቢቶች ወደ ስታድየሙ የደረሱት መገኘት ከሚገባቸው 26 ያህል ደቂቃዎችን ያህል ዘግይተው ነበር። በዚህም ምክንያት ጨዋታው ከተያዘለት ሰዐት 12 ያህል ደቂቃዎችን ዘግይቶ እንዲጀመር ሆኗል፡፡ እንደተለመደው በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ በጀመረው እና በፌደራል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ በተመራው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። በተለይ የወንድሜነህ አይናለም እና ዮሴፍ ዮሀንስ ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንዲሁም አማራ ክሌመንትን የፈተኑ ጠንካራ ሙከራዎች የጨዋታው ገፅታዎች ነበሩ። በአንፃሩ ደደቢቶች ሽመክት ጉግሳን እና አቤል እንዳለን ማዕከል ያደረጉ የመስመር ላይ ኳሷችን ቢጠቀሙም የመጨረሻ የኳሶቹ ማረፊያ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ነበሩ።

ጨዋታው ልክ እንደተጀመረ 49ኛው ሰከንድ ላይ ጌታነህ ከበደ ከፋሲካ አስፋው የተቀበለውን ኳስ ቢያስቆጥርም በእጅ ነክተሀል በማለት የመሀል ዳኛው ሚካኤል  አርዐያ ፊሽካቸውን አሰምተዋል። ደደቢቶችም ግቧ በመሻሯ ተገቢ አይደለም በሚል ተቃውሞን አሰምተዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለ20 ደቂቃዎች ያህል ሁለቱም ቡድኖች የተመጣጠነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያሳዩ ቢሆንም በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ በማድረግ የበላይነቱን ሲዳማ ቡና ሲወስድ ፤ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ አማራ ክሌመንት ለግብ  የቀረቡ በርካታ ሙከራዎችን በማምከን ኮከብ ሆኖ ታይቷል፡፡ 13ኛው ደቂቃ ላይ በደደቢት የግብ ክልል የተገኘውን የቅጣት ምት ፍፁም ተፈሪ ለዮሴፍ ዮሀንስ ሰጥቶት ዮሴፍ ወደ ግብ አክርሮ ሲመታት አማራ ክሌመንት በአስደናቂ ሁኔታ መልሶበታል፡፡ ደደቢቶች በአንፃሩ አጨዋወታቸውን ቀየር በማድረግ በሁለቱ ኮሪደሮች እና በመሀል ሜዳ ላይ በሚገኙ ዕድሎች ጌታነህን ማዕከል ያደረጉ ኳሶችን ሲያደርሱት ጌታነህም ዕድሎቹን በቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክራቸውም የሲዳማው ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ በተደጋጋሚ ሲያከሽፍበት ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ አቤል እንዳለ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ቢመታትም መሳይ አያኖ አድኖበታል፡፡

አሁንም ተጭኖ በመጫወቱ የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳወቹ ሲዳማዎች 33ኛው እና 44ኛው  ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሀንስ በቀጥታ አክርሮ በመታቸው ኳሶች ሙከራ አድርገዋል። በሌላ አጋጣሚ ወንድሜነህ አይናለም ከቅጣት ምት በቀጥታ የሞከረው ኳስ በብርሀኑ ቦጋለ ተመልሶ ሀብታሙ ገዛኸኝ ጋር ቢደርስም የሀብታሙ ሙከራ በዛሬው ጨዋታ ኮከብ በነበረው ግብ ጠባቂው ክሌመንት አዞንቶ በአስደናቂ ጥረት ወጥቶበታል፡፡ በደስታ ደሙ እና አንዶህ ክዌኪ የተገነባው የደደቢት የተከላካይ አጥር በአዲስ ግደይ ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ በተደጋጋሚ ቢፈተንም የአንዶህ ክዌኪ እና አማራ ክሌመንት ድንቅ ብቃት ግን 3ቱ አጥቂዎች በቀላሉ ግብ ለማስቆጠር እንዲቸገሩ አድርጓል።

በደደቢቶች በኩል ደግሞ በየአብስራ ተስፋዬ ፣ ፋሲካ አስፋው እና ሽመክት ጉግሳ ጥረት አደገኛ የሆኑ ጥቃቶች ቢታዩም በቀላሉ በሲዳማ ቡና ተከላካዮች ሲመለሱ አስተውለናል። 40ኛው ደቂቃ ላይ አቤል እንዳለ ከማህዕዘን ያሻገራትን ኳስ ሽመክት ጉግሳ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራው የላይኛውን የግብ ብረት ታካ ወጥታበታለች ፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን በሲዳማ በኩል አማካዩ እና አምበሉ ፍፁም ተፈሪ በግሩም ሁኔታ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ እየገፋ በመግባት ወንድሜነህ አይናለም በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ አድርጎ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ደደቢቶች በጌታነህ ላይ አክዌር ቻሞን ጨምረው በማስገባት አሰላለፋቸውን ከ4-5-1 ወደ 4-4-2 ቀይረው ሲገቡ ሲዳማ ቡናዎች ግን ምንም ለውጥ በዛው የ4-3-3 አሰላለፍ ከእረፍት ተመልሰዋል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ሀብታሙ ገዛኸኝ በቅፅበት በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ የመታትን ኳስ አማራ ክሌመንት አሁንም ሊያድንበት ችሏል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ አይናለም ከማዕዘን ምት የላካትን ኳስ አዲስ ግደይ በግንባሩ ሲገጭ አሁንም አስደናቂ የነበረው ክሌመንት እንደምንም አውጥቶበታል፡፡ ደደቢቶች በተደጋጋሚ በእለቱ ዳኛ ሚካኤሌ ውሳኔወች ደስተኛ ባለመሆን ተቃውሞን ሲያሰሙም ነበር፡፡ 61ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ለአቤል እንዳለ የሰጠውን ኳስ አቤል ወደ ሳጥኑ እየገፋ በመግባት አሻምቶት ጌታነህ ከበደ  ወደ ግብ ቢሞክርም ተከላካዩ ግሩም አሰፋ ተንሸራቶ አስጥሎታል፡፡ ቀሪዎቹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች በተወሰነ መልኩ የኃላ በራቸውን ሸፍነው ግቧን አስጠብቀው ለመውጣት ጥረት ያደረጉበት ደደቢቶች ደግሞ ምንም እንኳን መልካም አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ወደ ግብ ለመለወጥ ያደረጓቸው ጥረቶች ዝቅተኛ የነበሩበት ሆኖ ተጨማሪ ግቦችን ሳንመለከት ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በውጤቱም ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድል ሲያስመዘግብ ደደቢት በሁለተኛው ዙር ከሜዳው ውጭ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ተስኖታል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ጨዋታው ጥሩ ነበር። የመጀመሪያዎቹን 10 ደቂቃዎች  ልክ አልነበርንም ፤ የአቋቋም ችግር ነበረብን። ግብም ለማስተናገድ ተቃርበን ነበር። ነገር ግን ከአስሩ ደቂቃዎች በኃላ እየተደራጀን በመምጣት ለማስተካከል ሞክረናል። በተሰጠብንም ፍፁም ቅጣት ምት አልተረበሽንም። ግብም ቢቆጠርብንም ቀደሞም ሙሉ በራስ መተማመን ነበረን። ፍፁም ቅጣት ምቷ ከተሳተች በኃላ ግን እኛ መአት አጋጣሚ አግኝተናል። ሚፈለገውን ሶስት ነጥብ ይዘንም ወጥተናል። አሁንም ግን አጨራረሳችንን ማስተካከል አለብን፡፡

ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

ጨዋታው አሪፍ ነበር። ያው ሁሌም በዳኛ ስህተት ተሸንፈን እየወጣን ነው። እንግዲህ ምንም ማድረግ አንችልም ተሸንፈን ወጥተናል፡፡ የገባ ጎል ተሻረብን ፤ ብዙ ጫና ነበር የደረሰብን። አላስፈላጊ ካርዶችም ይታዩ ነበር።