የ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን እንቆቅልሽ እስካሁን አልተፈታም

ባሳለፍነው ሳምንት ፍፃሜውን ባገኘው እና ቡሩንዲ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ከ17 አመት በታች የሴካፋ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ በውድድሩ ረጅም ርቀት ይጓዛል ተብሎ ቢጠበቅም ሦስት ተጨዋቾች መጫወት በሚያስችላቸው እድሜ ላይ ተገኝተው ሳለ በፓስፖርት አወጣጥ ስህተት ምክንያት የሴካፋ ዲሲፒሊን ኮሚቴ የኢትዮዽያ ሦስት ተጨዋቾችን ከውድድሩ ውጭ በማድረግ የ5ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት መቅጣቱን ተከትሎ በቡድኑ ውስጥ በተፈጠረው አለመረጋጋት ከውድድሩ በጊዜ ተሰናብቶ መመለሱ ይታወቃል። 

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተፈጠረውን ስህተት አጣርቶ አጥፊውን አካል በመለየት አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ ከዚህ ቀደም ለሶከር ኢትዮጵያ ቢገለፅም እስካሁን ምንም አይነት የእርምት እርምጃ ሳይወስድ ዝምታን መርጧል። 

ከፌዴሬሽኑ ባገኘነው መረጃ መሰረት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ  አጣሪ ኮሚቴ በመሰየም የችግሩን መንስዔ እያጣራ ይገኛል። አጣሪ ኮሚቴውም ጉዳዩን አጣርቶ መጨረሱ ቢነገርም ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ በሰሞኑ ስብሰባዎች በመጠመዱ ምክንያት ውሳኔው እንደዘገየና በቅርቡ ከውሳኔ እንደሚደረስ ሰምተናል።