ከፍተኛ ሊግ | በአንደኛው ዙር ምድባቸውን በቀዳሚነት ላጠናቀቁ ቡድኖች ሽልማት ተበርክቷል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ ተጀመሮ የአንድ ሳምንት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ በየምድባቸው በቀዳሚነት ያጠናቀቁት ባህርዳር ከተማ እና ሀላባ ከተማ ለቡድኖቻቸው የማበረታቻ ሽልማት አበርክተዋል።

በ35 ነጥቦች የምድብ ሀ መሪነትን የያዘው ባህርዳር ከተማ ትላንት ምሽት በባህርዳር ብሉ ናይል ሆቴል እና ስፓ ለቡድኑ ተጫዋቾች እና ለአሰልጣኝ ክፍል ኃላፊዎች የማበረታቻ ሽልማት የመስጠት እና የምስጋና ዝግጅት ተከኗውኗል።

በሃበሻ ቢራ ስፖንሰርነት ከ12 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው ዝግጅት የከተማው ምክትል ከንቲባን ጨምሮ የክለቡ አመራሮች፣ ተጨዋቾች፣ ደጋፊዎች እና ዝግጅቱን ያዘጋጀው የሃበሻ ቢራ እንግዶች በቦታው የተገኙ ሲሆን የእራት ግብዣ እና የሽልማት አሰጣት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል። ዝግጅቱን በንግግር የከፈቱት የባህርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ክብረት ሙሐመድ በክለቡ የመጀመሪያ ዙር እንቅስቃሴ መደሰታቸውን በመግለፅ ለተጨዋቾቹ እና ለአሰልጣኝ ክፍል ሃላፊዎች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ደጋፊዎችንም በድንቅ ድጋፋቸው አማካኝነት ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።”ባህር ዳር ከተማ ድንቅ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ነው። ይህንን ደግሞ እንደ በጎ መጠቀም አለብን። ቡድኑን እንደ 12ኛ ተጨዋች በመሆን ሁልግዜ መደገፍ እና ማበረታታት አለብን።” ብለዋል። አቶ ክብረት ጨምረው ቡድኑ በፋይናንስ ደረጃ እንዲጠናከር በከተማው ያሉ ባለ ሀብቶች በአቅማቸው ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጥሪ አስተላልፈዋል።

በመቀጠል የሽልማት ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን የባህርዳር እና አካባቢዋ የሃበሻ ቢራ አከፋፋይ የሆኑት ኢ/ር ንግሩ ሙሉዓለም ከሽልማቱ በፊት ንግግር ካደረጉ በኃላ ለቡድኑ የ250 ሺ ብር ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን በቀጣይም ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ከዚህ የተሻለ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በሃበሻ ቢራ ስም ተናግረዋል። ኢ/ር ንግሩ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያድግ ከሆነ አዲስ አበባ በሚገኘው የግል ድርጅታቸው ስም 300ሺ ብር ለቡድኑ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

ከሽልማቱ በኃላ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው የተሰማቸውም ስሜት ለታዳሚያኑ ያጋሩ ሲሆን በተደረገላቸው ነገር ሁሉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። ሃበሻ ቢራ ለቡድኑ ካበረከተው የገንዘብ ሽልማት ውጪ ለደጋፊ ማህበሩም 9 ሜትር በ50 ሜትር የሚሆን የባህርዳርን ክለብ አርማ የያዘ የድጋፍ መስጫ ባነር ማሰራቱን እና በስጦታ መልክ ማበርከቱን በወኪሉ አማካኝነት አስታውቋል።

በ31 ነጥቦች የምድብ ለ ሰንጠረዥን የሚመራው ሀላባ ከተማም ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ለቡድኑ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል። በሲና ካፌ እና ሬስቶራንት በተከናወነው ዝግጅት ላይ የሀላባ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኑር ሳሊያና የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሱልጣን ጁሀር እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የ200 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቷል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ለዚህ ውጤት ላበቁት የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሚሊዮን አካሉና ምክትሎቻቸው፣ ለቡድን መሪው አቶ አፈወርቅ ታምራት እንዲሁም የቴክኒክ ኮሚቴውና ለክለቡ ተጫዋቾች በሀላባ ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበው ሽልማቱን አበርክተዋል።