የፌዴሬሸኑ ምርጫ ቀን እና ቦታ ነገ ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ሂደት ከታሰበበት ከመስከረም 30 አንስቶ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እየተንጓተተ የችግሩ መጠን እየተባባሳ መሄዱን ከግምት ያስገባው የእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ ሁለት አጣሪ ኮሚቴ ወደ ኢትዮዽያ በመላክ ያለውን ሁኔታ የሚመለከታቸውን አካላት በቡድን እና በተናጥል ካወያየ በኋላ ለችግሩ መንስዔ ናቸው ያላቸውን የአስመራጭ ኮሚቴ እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ገለልተኛ አይደሉም በማለት እንዲፈርስ ያደረገ ሲሆን  የምርጫ ማስፈፀሚያ ደንቡ ግልፅ አይደለም በሚል አዲስ የምርጫ ማስፈፀሚያ ባለ ሰባት አንቀፅ ደንብ ፊፋ መላኩ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ቅዳሜ ሚያዚያ 27 በካፒታል ሆቴል በማድረግ በቀረቡት ሁለት መሰረታዊ አጀንዳዎች ከውሳኔ ደርሷል። በዚህ መሰረት የምርጫውን ሂደት የሚቆጣጠር ከፊፋ የተላከውን የምርጫ ደንብ አፅድቋል። አዲስ አምስት አባላት ያሉት የምርጫ አስፈፃሚ እና ሦስት አባላት ያሉት የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መርጧል።

አዲስ የተመረጡት የምርጫ አስፈፃሚ አካላት  ከጠቅላላ ጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ የመጀመርያ ውይይታቸውን በዛው ካፒታል ሆቴል ያደረጉ ሲሆን ነገ ማምሻውን ሌላ ስብሰባ እንደሚቀመጡ ሰምተናል። በስብሰባቸው በርካታ ርዕሶችን በማንሳት ይወያያሉ ተብሎ ሲጠበቅ በዋናነት የምርጫው ቀንና ቦታ ይወስናሉ ፣ ክልሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ እጩ ፕሬዝደንት እና ስራ አስፈፃሚ አባላት እንዲልኩ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም መሰረት ሶከር ኢትዮዽያ እንዳገኘችው መረጃ አንዳንድ ክልሎች ቀድሞ እጩ ያደረጓቸው ግለሰቦችን ሙሉ ለሙሉ ሊቀይሩ የሚችሉ ሲሆን በአንፃሩ አንዳንድ ክልሎች ቀድመው የላኩትን እጩዎች ዳግመኛ ይልካሉ ተብሎ ይጠበቃል።