በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ የሚያተኩረው የምክክር መድረክ በአዳማ ተጀመረ

የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ከኦሎምፒክ ኮሚቴ በጋር በመተባበር በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ለሁለት ቀን የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ከረዩ ሆቴል ተጀምሯል።

የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ፣ የክልል ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ፣ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ የስራ እርከን የሚገኙ ኃላፊዎች ፣ የሁሉም ሊግ የክለብ ስራ አስኪያጆች ፣ አሰልጣኞች ፣ ተጨዋቾች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች እና የሚዲያ አባላት ተገኝተዋል። በዚህ የምክክር ጉባዔ ላይ መርሀግብሩ የተዘጋጀበትን አላማ የዕለቱ የክብር እንግዳዎች የሆኑት አቶ ርስቱ ይርዳው የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር እና አቶ አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት የገለፁ ሲሆን የስፖርታዊ ጨዋነት መደፍረስ አንገብጋቢ መሆኑን ፣ የሀገርን መልካም ስም እያጎደፈ ፣ ሰውን ለጉዳት እየዳረገ ፣ ንብረት እያወደመ መሆኑን ፤ ይህን አሳሳቢ ችግር እንዳይባባስ በዘላቂነት ለመፍታት ይህ ጉባኤ መካሄዱን ገልፀው በውይይቱ መልካም ነገሮችን በማንሳት ወደ መፍትሄ እንዲመጡ አሳስበዋል።

በጉባዔው ላይ የተካፈሉትን አካላት ቀልብ የገዛው በዶ/ር አያሌው ጥላሁን የቀረበው ጥናታዊ ፁሁፍ ሲሆን በጥናታዊ ፁሁፋቸው የችግሮች መንስኤዎች ያሉቸውን ነጥቦች በግልፅ በዝርዝር አቅርበዋል። ለአብነት ያህል:-

በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በኩል

ችግሮችን እያየ ዝምታ መምረጡ ፣ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተቀራርቦ አለመስራቱ ፣ ፌዴሬሽኖችን የሚቆጣጠርበት መንገድ ደካማ መሆኑ ፣ በጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍና ክትትል አለማድረግ

በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ በኩል

አለም አቀፍ ህጎችና ደንቦችን ሳይሸራረፍ ተግባራዊ አለማድረጉ ፣ በፌዴሬሽኑ የተዋቀሩ የዳኞች ፣ የውድድር ፣ የፀጥታ ፣ የዲሲፒሊን እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት እና አሰራር ፍፁም ባህላዊ መሆን ፣ ጥፋት በሚፈፅሙ ክለቦች ላይ የሚወስደው እርምጃ ጠንካራና ሌሎችን የሚያስተምር አለመሆን እና የውሳኔዎች ወጥ አለመሆን


በክለቦች በኩል

የክለቦች አደረጃጀት እና አሰራር በሰዎች ፍላጎት እንጂ አለም አቀፍ መመርያን ደንብን ተከትሎ አለመሆን ፣ የክለብ አመራሮች ሰለ እግርኳስ ያላቸው ግንዛቤ ውስንነት ያለው መሆኑ ፣ የክለብ አመራር አካላት በማንኛውም ሁኔታ ውጤቱን ማግኘት እንጂ ለስፖርቱ ፣ ለተመልካቹ ፣ ለተጫዋቾችና ለሚዲያው የማይጨነቁ መሆናቸው።
በአሰልጣኞች በኩል
ከወቅታዊ የእግርኳስ ህጎች ጋር ራስን አለማዘጋጀት ፣ የዳኝነት ውሳኔንና የጨዋታ ውጤትን በፀጋ አለመቀበል ፣ ተጨዋቾችን መቆጣጠር አለመቻላቸው ፣ ራሳቸው የችግሩ አካል መሆናቸው ፣ ውጤት ሲጠፋ ውጫያዊ ስበቦችን መፍጠር ።


በተጨዋቾች በኩል

የእግርኳስ ህግ ግንዛቤ አለመኖር ፣ ለስፖርቱ እና ለራሳቸው ክብር ዋጋ አለመስጠት ፣ ስሜታዊነት ፣ ተመልካቾች እና ደጋፊዎችን ለፀብ ማነሳሳት ፣ ያልተገባ አጨዋወት በመጠቀም ጉዳት በማድረስ የጨዋታውን መንፈስ ማደፍረስ ፣ በክለብ አመራሮች ለፀብ ተጠምዝዞ መምጣት

በዳኞች በኩል

በአካል ብቃት ማነስና የስነ ልቦና ዝግጅት አለማድረግ ፣ ከውድድር በፊት ከክለብ አመራሮች ጋር አላስፈላጊ ግንኙነቶች ማድረግ ፣ የፍትሀዊነት ችግር ፣ በዳኞች በኩል ተናቦ ጨዋታዎችን የመምራት ችግር ።

በመገናኛ ብዙሃን በኩል
አንዳንድ የሚዲያ አካላት የሚያቀርቡት ዜና ሚዛናዊ አለመሆን ፣ በሜዳ ላይ የተሰራውን ስህተት እና ፌዴሬሽኑ የሚሰጠውን ውሳኔ መቃወም ፣ የችግሮች መፍትሄ አለመሆን።

በፀጥታ አካላት በኩል

የክለባዊ  ፣ ክልላዊ ስሜቶች መደገፍ መጀመራቸው ፣ ሁኔታዎችን በቸልተኝነት ማየት ፣ ስለስፖርት ደህንነት ጥልቅ ግንዛቤ አለመኖር

በእነዚህ አካላት ላይ ዶ/ር አያሌው ጥናታዊ ፅሁፋቸውን አጠቃለው በዋናነት ያሰመሩበት የዘረኝነት ብሄርተኝነት ስሜት በእግርኳሱ ውስጥ መግባት ትልቁ ችግር መሆኑን አሳስበው በውይይት መድረኩ ላይ በግልፅ እንዲወያዩበት አፅኖት ሰጥተው አልፈዋል።

ከምሳ እረፍት በኋላ ከሰአት በቀጠለው በአራት ግሩፕ በተከፈለው የውይይት መድረክ ላይ ሁሉም ተሳታፊ አካላት እስከ ማምሻው ድረስ በግልፅ አሉ የሚባሉ ችግሮችን በማንሳት ሲወያዮ አርፍደዋል። በመጨረሻም በተነሱት ችግሮች መንስኤ እና መፍትሄ ላይ የሚነሱ ሀሳቦች ሳይጠቃለሉ ወደ ነገ ለይደር ተሻግረዋል።

የምክክር ጉባኤው ነገ ሲቀጥል በቀረቡት የውይይት ሀሳቦች ላይ ማጠቃለያ ተሰጥቶ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ የጉባኤው ፍፃሜ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።