አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከሦስት ወራት ቅጣት ስለመመለሳቸው ይናገራሉ

በ13ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ደደቢት ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ  2-1 ከተረታበት ጨዋታ በኋላ የደደቢቱ ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በዕለቱ ዳኛ ላይ የሰነዘሩትን አስተያየት ተከትሎ የጨዋታው ኮሚሽነር ባቀረበባቸው ሪፖርት መነሻነት የዲሲፕሊን ኮሚቴ በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ላይ የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና ለ3 ወር ያህል ቡድኑን እንዳይመሩ በማለት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል።

ውሳኔውን ተከትሎ ደደቢት ከ15ኛ ሳምንት ከመከላከያ ጨዋታ ጀምሮ ያለፉትን 3 ወራት ያህል በምክትል አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ ሲመራ ቆይቷል። ያለ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ቡድኑ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎችም ሁለት ጨዋታ ብቻ አሸንፎ በአንድ ጨዋታ አቻ በመውጣት በአምስት ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዶ ከመሪነት ደረጃው በመንሸራተት በአሁኑ ወቅት በ33 ነጥብ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል  ።

አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የተጣለባቸውን የሦስት ወር ቅጣት አጠናቀው በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ በአዲስ አበባ ስታድየም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ቡድኑን እየመሩ ወደ ሜዳ የሚገቡ ይሆናል። ቡድኑን ባልመሩበት ወቅት ውጤት ርቆት የቆየው ደደቢት ያሳለፈውን ጊዜ አስመልክቶ እና ዳግም ቡድኑ ወደ ጥንካሬው ለመመለስ በቀሪ ጨዋታዎች ያሰቡትን እቅዳቸውን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ ይህን ብለዋል።

” የሀገራችን እግርኳስ ችግር እንዳለበት ይታወቃል። በፌዴሬሽኑ ውድድር የመምራት አቅም ማነስ ምክንያት በየሄድንበት ቦታ ይፈጠር የነበረ ችግር የሚያስተካክል እና ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ ያ ምሬት ነው እንደዛ እንድናገር ያደረገኝ ፤ አሁንም ቢሆን እንቆቅልሹ አልተፈታም። ቡድኑን ጎድቼዋለው ብዬ በራሴ በጣም ተሰምቶኛል። ውጭ ሆነህ እና ውስጥ ሆነህ 100% በጣም ልዩነት አለው። ከላይ ቁጭ ብለህ የቱንም ያህል ታክቲካል ነገር ብትናገር አንተ ቆመህ እንዳለው አይደለም። በሙያው ስነ ምግባር በልምምድ ወቅት የአሰልጣኝ 95% ይወስዳል ተጫዋቹ 5% ነው ። ወደ ጨዋታ ስትገባ ደግሞ ያንን ነው የምትገለብጠው 95% ለተጫዋቾቹ ሰጥተህ  5% የአሰልጣኝ ነው ። የሰጠሀቸውን ታክቲክ እንዲተገብሩ ቆመህ ታደራጃለህ። ቁጭ ብለህ ስታይ ክፍተቶች አጉልቶ ያሳያሀል። ችግሮችን ከታች ሆኜ ባለማስተካከሌ በጣም በጣም ውስጤ ተጎድቷል። አሁን ተመልሻለው ፤ ብዙ ክፍተቶችን አይቻለው። እነዚህ ክፍተቶች በሚገባ አስተካክለን ቡድኑን አጠናክረን ወደ አሸናፊነት በመመለስ የተሻለ ነገር ለማድረግ ጥረት አደርጋለው። “