የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለስፖርት ህክምና ባለሙያዎች ተሰጠ

ስፓይን ስፖርት ኮንሰልታንሲ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በትብብር ያዘጋጁት በመጀመሪያ እርዳታ ላይ ሙሉ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና ሰኞ ግንቦታ 13 – አርብ ግንቦት 17 ድረስ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ለስፖርት ክለብ የህክምና ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል የህክምና ባለሙያዎች እና ሎሎች በህክምና ዘርፍ ሙያ ላይ ባሉ ባለሙያዎች የተሰጠ ነበር፡፡ በስልጠናው ላይ የቡራዩ ከተማ እና ደደቢት ክለብ የህክምና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን እንደስፓይን ስፖርት ኮንሰልታንሲ ዋና ስራ-አስኪያጂ ዮናስ አለማየሁ ገለፃ ከሆነ አብዛኞቹ ክለቦች በውድድር ላይ መገኘታቸው በስልጠናውን ላይ እንዳይካፈሉ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡ አቶ ዮናስ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት ይህ ስልጠና ሲደረግ ለአምስተኛ ግዜ ነው፡፡ ከዚህ አስቀድሞም ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ቂርቆስ በስልጠናው ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡

ስልጠናው በእግርኳስ ሜዳዎች ላይ ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ አደጋዎች እና ጉዳቶች እንዴት ተጨማሪ ጉዳት ሳይከሰት እርዳታ መስጠት እንደሚቻል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ስልጠናውን ከሰጡ ባለሙያዎች መካከል የሆኑት ዴቪድ ጃንሰን በስፖርት ህክምናው ዘርፍ ተጨማሪ ስልጠናዎች እንደሚያስፈግ ገልፀዋል፡፡ “ካየሁት ነገር ተነስቼ ተጨማሪ ስልጠናዎችን ያስፈልጋሉ፡፡ የእግርኳስ ክለቦች ወገሻዎች በዚህ ስልጠና ላይ በብዛት እንደሚገኙ ጠብቄ ነበር ምክንያቱም ስልጠናውን በጣም አስፈላጊ ስለሆነ፡፡ ህክምና አስፈላጊ ነው፡፡ ክለቦች የተጫዋቾቻቸውን ጤና መጠበቅ ካልቻሉ ተጫዋቹ በፍጥነት ከጉዳት ማገገም አይደለም ጥሩ መንቀሳቀስ ራሱ አይችልም፡፡”

እንደኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ህክምና ኮሚቴ መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አባዛኞቹ ክለቦች ትክክለኛ የህክምና ባለሙያ የላቸውም፡፡ ይህ ጉዳይ እንደሚያሳስበው የደደቢት እግርኳስ ክለብ የህክምና ክፍል ሃላፊ ኡስማን ሰዒድ ይናገራል፡፡ “ይህ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች ወደ እግርኳሱ እየመጡ አይደለም፡፡ የጤና ባለሙያዎች ሳይሆኑ በቦታው እየሰሩ የሚገኙት በልምድ ያገኙትን እውቀት ይዘው የሚሰሩት ይበረክታሉ፡፡ በውጪው አለም የስነ-ልቦና፣ የህክምና እና የስነ-ምግብ ባለሙያዎች አሉ እኛ ጋር ግን ሃኪሙም፣ ወጌሻውም አንተ ነህ፡፡”

በሜዳ ላይ የሚያጋጥሙ ጉዳቶች በአብዛኛው የሚሰጡ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታዎች ጥብቅ ክትትል እና ስራ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ሰፊ ትኩረት የማይሰጣቸው የዝቅተኛ ሊጎች፣ የሴቶች እና የታዳጊዎች ውድድሮች ላይ እንደነዚህ ዓይነት ጉዳቶች አፋጣኝ የሆነ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ አሰጣጡ ችግር በስፋት ይታያል፡፡ ይህ ስልጠናም ይህንን ችግር ከማቀለል እና ከመፍታት አንፃር የተዘጋጀ ነው፡፡