ሆሳዕና ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መግባቱን አረጋገጠ

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ሆሳእና ከነማ ሃላባ ከነማን 3-0 አሸንፎ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መግባቱን አረጋግጧል፡፡

የሀላባ ከነማ ደጋፊዎች የቡድናቸውን ወሳኝ ጨዋታ ለመከታተል ወደ ድሬዳዋ በሚያመሩበት ወቅት አሰበ ተፈሪ ላይ በደረሰ አደጋ 4 ደጋፊዎች ህወታቸው ማለፉን ተከትሎ ጨዋታው በ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተጀምሯል፡፡

ሆሳእና ከነማ በወሳኝ ተጫዋቾቹ ግቦች ታግዞ 3-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ዱላ ሙላቱ በ45ኛው ቴዎድሮስ መንገሻ በ64ኛው እንዲሁም ተዘራ አቡቴ በ82ኛው ደቂቃ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡ የዛሬዎቹ ግቦች በአጠቃላዩ ውድድር ለተዘራ 4ኛ ፣ ለቴዎድሮስ 3ኛ እንዲሁ ለዱላ 2ኛ ግባቸው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የሆሳእና ከነማው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ሃላባ ከነማን ማወቃቸው ጨዋታውን ለማሸነፋቸው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ ሃላባ ከነማ በዞናችን የሚገኝ ቡድን በመሆኑ ስለ አጨዋወታቸው እናውቃለን፡፡ ከጨዋታው በፊትም አሸንፈናቸው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደምናልፍ እርግጠኞች ነበርን፡፡ ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረን አሸንፈን ወጥተናል›› ብለዋል፡፡

dd

የጨዋታውን ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረው ቴዎድሮስ መንገሻ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በስፖርት ኮሚሽን እና ወጣቶች ቢሮ በጋራ ተመርጧል፡፡

በመጪው እሁድ ከሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ አሸናፊ ጋር የፍፃሜ ጨዋታውን የሚያደርገው ሆሳዕና ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያልፍ በታሪኩ ለመጀመርያ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሃድያ ዞን ወደ ፕሪሚየር ሊግ የገባ የመጀመርያው ክለብ ለመሆን በቅቷል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ በመሳተፍ ደግሞ 43ኛው ክለብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *