በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ሆሳዕና ከነማ ሃላባ ከነማን 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል፡፡ በክለቡ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳለፍ ታሪክ የሰሩት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ስለ ድላቸው ምስጢር እና የተሰማቸውን ስሜት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ይህንን ቡድን ላለፉት 9 አመታት አሰልጥኘዋለሁ፡፡ የአመታት ህልሜ የነበረው ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማሳደግ ነበር፡፡ ዛሬ ያ የአመታት ህልሜ ተሳክቶልኛል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
አሰልጣኙ አክለውም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ያበቃቸውን ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ የድላችን ምስጢር በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ቡደን መገንባታችን ነው፡፡ የተጫዋቾቼ የማሰነፍ ፍላጎትና ተነሳሽነት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንድናድግ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ከተጫዋቾቹ ጋር ለበርካታ አመታት ስለሰራሁ አጨዋወታቸውን ና ፍላጎታቸውን በቀላሉ እረዳለሁ፡፡ በደምብ ስለተዋሃድን የምንፈልገውን ስኬት እንድናመጣ አስችሎናል፡፡›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ቡድኑ ለከርሞ በሚወዳደርበት ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ፈተና ይገትመዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሰልጣኙም ወደመጡበት ተመልሰው ላለመውረድ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ቡድናችን የተሟላ ነው ማለት አልችልም፡፡ ገና ብዙ መስራ ያሉብን ነገሮች አሉ፡፡ ወደመጣንበት ላለመመለስ እና በሊጉ ለመቆየት ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ተዘጋጅተናል፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡