ከፍተኛ ሊግ ለ | መሪው ሀላባ ሲሸነፍ ተከታዩ ደቡብ ፖሊስ ድል አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 18ኛ ሳምንት ዛሬ በተካሄዱ 4 ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ መሪው ሀላባ ከተማ ሽንፈትን ፣ ተከታዩ ደቡብ ፖሊስ ድል ፣ ፍፁም ደስይበለው ደግሞ ሐት-ትሪክ ያስመዘገበበት እለት ሆኖ አልፏል። 

ደቡብ ፖሊስ 2-1 ዲላ ከተማ

(በቴዎድሮስ ታከለ)

በምድብ ለ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ደቡብ ፖሊስ እና ዲላ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ እና እጅግ ማራኪ እና ውብ እንቅስቃሴ ታይቶበት በደቡብ ፖሊስ 2-1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ 15 ደቂቃዎች የተሻለ የጨዋታ አቀራረብ የነበራቸው ደቡብ ፖሊሶች 10ኛው ደቂቃ ላይ በፊት መስመር ላይ ተሰልፎ በዲላ ተከላካዮች ላይ ጫና ሲፈጥር የነበረው ኬንያዊው አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ በግራ በኩል ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አማካዩ አበባየሁ ዮሀንስ ግብ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሆነዋል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ዲላዎች መና በቀለ በመስመር በኩል እየገባ ምትኩ ማመጫ በመሀል ሜዳ እና ሄኖክ አየለ በፊት መስመር ላይ በርካታ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ኳስና መረብን በቀላሉ ማገናኘት ግን አልቻሉም። በደቡብ ፓሊስ በኩል ደግሞ ዱላ ሙላቱ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ሳጥን እየገባ ተደጋጋሚ እድሎችን ቢያገኝም በቀላሉ ሲያመክን ተስተውሏል። በ39ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ዮሀንስ ከቅጣት ምት ያሻገራትን ኳስ ኤሪክ ሙራንዳ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት በደቡብ ፖሊስ ፤ በ41ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ማራኪ ቅብብል ምትኩ ማመጫ ከኤልያስ እንድሪያስ ጋር ተቀባብሎ ኤልያስ በቀጥታ መትቷት ግብ ጠባቂው መኳንንት አሸናፊ ሲመልሳት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ አማካይ ታዲዮስ አንበሴ አክርሮ መትቶ አግዳሚውን ጨርፋ የወጣችው ደግሞ በዲላ በኩል በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።

ሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ በሚባል እንቅስቃሴ ቢጀምርም ዲላ ከተማዎች በተሻለ መልኩ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የእንቅስቃሴ የበላይነት የወሰዱበት ነበር። በ48ኛው ደቂቃ ላይ ምትኩ ማመጫ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አምበሉ ሳሙኤል በቀለ ሞክሮ በቀጥታ በግብ ብረት ሲመለስበት በ52ተኛው ደቂቃ ላይ ግን በመጀመሪያው አጋማሽ በጉዳት ኤልያስ መንግስቱን ተክቶ የገባው እስጢፋኖስ የሺጌታ በግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ዲላ ከተማን የተቀላቀለው ሄኖክ አየለ ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ዲላን አቻ አድርጓል፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላም ዲላዎች በተሻለ መልኩ በመስመር እና መሐል ለመሐል በተደጋጋሚ ወደ ደቡብ ፖሊስ የግብ በር ሲደርሱ ደበብ ፓሊሶች ኤሪክ ሙራንዳ እና ብርሀኑ ላይ ትኩረት ያደረገ የመስመር አጨዋወትን ተከትለዋል።  66ተኛው ደቂቃ ላይ በመሀል ሜዳ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ምትኩ ማመጫ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ታዲዮስ አንበሴ ወደ ግብ አክርሮ መቷት መኳንንት አሸናፊ እንደምንም መልሶበታል። በደቡብ ፖሊሶች በኩል ደግሞ 68ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ደረጀ ፍሬው በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወታበታለች።

በዲላ ከተማ ብልጫ የተወሰደባቸው ደቡብ ፖሊሶች የማታ የማታ ድል ያስመዘገቡበትን ጎል አግኝተዋል። በ84ኛው ደቂቃ ኤሪክ ሙራንዳ እየገፋ ወደ ሳጥን ጠርዝ ተጠግቶ አክርሮ የመታትን ኳስ የዲላ ከተማው ግብ ጠባቂ ተካልኝ ኃይሌ ኳሷን ለመያዝ ሲሞክር በመልቀቁ ምክንያት አጠገቡ የነበረውና መቐለ ከተማን ለቆ ደቡብ ፖሊስን የተቀላቀለው ዱላ ሙላቱ ወሳኟን የድል ጎል አስቆጥሯል። የዲላ ከተማው ም/አሰልጣኝ ምንተስኖት መላኩ ከደጋፊዎች ጋር የሚፈጥረው ለፀብ የሚያነሳሱ ምልልሶች እና የምልክት ስድቦች ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ የተፈጠረ ያልተገባ ድርጊት ነበር።

ሀምበሪቾ 3-2 ሻሸመኔ ከተማ
(በአምሀ ተስፋዬ)

የቀድሙ ቡድኑን ለመጀመርያ ጊዜ በተቃራኒነት በገጠመው ያሬድ አበጀ የሚመራው ሀምበሪቾ በፍፁም ደስይበለው ልዩ ብቃት ታግዝ.ዞ ሻሸመኔ ከተማን አሸንፏል። በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ውስጥ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እንግዶቹ ሻሸመኔዎች ሁለት ግቦችን በአምስት ደቂቃ ልዩነት በማስቆጠር 2-0 መምራት ችለው ነበር። በ12ኛው ደቂቃ አብርሃም አለሙ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ወደግብነት ለውጦ ሻሸመኔን ቀዳሚ ማድረግ ሲችል በ17ኛው ደቂቃ በድጋሚ አብርሃም አለሙ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ ወደግብ አክርሮ በመምታት ሁለተኛውን አክሏል።

በተከተታይ ግብ የተቆጠረባቸው ሀምበሪቾዎች ውጤቱን ለማጥበብ ጥረት ሲያደርጉ በ28ኛው ደቂቃ ፍፁም ደስይበለው ላይ በተሰራው ጥፋት ላይ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ፍፁም ደስይበለው በመምታት ወደግብነት ለውጦታል። ከግቡ መቆጠር ባኋላ በሁለቱም መስመር የሚጫወቱት አገኘው ላይራ እና ምኞት ማርቆስ ኳስ በረጅሙ ወደግብ ክልል በማሻማት የሻሸመኔን የተከላካይ ቡድን ቢፈትኑም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በሻሸመኔ መሪነት ዕረፍት ወጥተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሀምበሪቾ በተደጋጋሚ ረጅም ኳስ ወደፊት በመጣል ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በፍፁም ደስይበለው ብቃት ታግዘው ድል ቀንቶቸዋል። በ47ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ላይ አገኘሁ ተፈራ ያሻማውን ኳስ ፍፁም ደስይበለው ከሁለት ተከላካዮች ማሀል በመውጣት ለመሬት የተጠጋችውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ከአቻነት ግቡ በኋላ ሀምበሪቾዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የበለጠ ጫና ሲፈጥሩ በተቃራኒው ሻሸመኔዎች አንድ ነጥቡን ለማስጠበቅ በሚመስል መልክ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው ተስተውለዋል። በ58ኛው ደቂቃ አሸናፊ አዳሙ ወደግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ተከላካይ ክፍል ደርሱ ቢደረብም ኳስ አቅጣጫዋን በመቀየር ወደፍፁም ደስይበለው ያመራች ሲሆን ፍፁም ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ግብነት በመቀየር ለራሱ እና ለቡድኑ ሶስተኛ ግብ በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሰርቷል።

በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም በኩል ሙከራዎች ታይተዋል። በ67ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል በመግባት አሸናፊ አደም ያባከነው እንዲሁም በተመሳሳይ ቴዴ ታደሰ ያመከነው ኳስ የሀምበሪቾን የግብ ልዩነት ከፍ ማድረግ የሚያስችሉ እድሎች ነበሩ። በሻሸመኔ በኩልም የፊት መስመር ተሰላፊያቸው አብርሃም ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ያደረገው የተናጠል ጥረት የሚደነቅ ነበር።

ሌሎች ጨዋታዎች 

መሪው ሀላባ ከተማ ወደ ድሬዳዋ አቅንቶ በናሽናል ሴሜንት ሽንፈት ገጥሞታል። በናሽናል ሴሜንት 1-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ታጅሮ ጃፈር የብቸኛው ጎል ባለቤት ነው። መቂ እና ቡታጅራ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የምድብ ለ 18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገ ይቀጥላል

የደረጃ ሰንጠረዥ

ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች