” ጥያቄያችን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ግልፅ አሰራር እንዲከተል ነው” ሚካኤል አርዓያ 

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በወልዋሎ ላይ የተጣለውን ቅጣት በከፊል የሻረበትን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር ” ውሳኔው ምክንያት በግልፅ አልተብራራም” በሚል በቅሬታ ደብዳቤ መገለፁ ይታወሳል። ከወቅታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ከሁለት ሳምንታት በፊት ውድድሮች እስከማቆም ከደረሱበት ውሳኔ እና አዲሱ የፌዴሬሽን ምርጫ ጋር የተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌዴራል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።


ከወልዋሎ የይግባኝ ውሳኔ በኋላ ዓርብ እለት ያወጣችሁት የቅሬታ ደብዳቤ ላይ ከሰፈረው በተጨማሪ የእግርኳሱ ማኅበረሰብ እንዲረዳችሁ የምትፈልጉት ዓብይ ጉዳይ ምንድን ነው?


★ የደብዳቤውን አላማና አቅጣጫ በሚመለከት በሬድዮ ስትወያዩበት ስለሰማው የእናንተ ሚዲያ በሚገባ ተረድቶታል ብዬ አስባለሁ፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈት ከሶስት አመት ጀምሮ እየተንከባለለ እዚህ ደረጃ የደረሰ ነው፡፡ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በሁለቱ ክለቦች የታየውም ችግር የመጣው በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡ እንደ ሙያ ማኅበር በዚህ ጉዳይ ቅሬታችንን አቅርበን ነበር፡፡ ክለቦችም የራሳቸው መብት ስላላቸው መሄድ እስከሚችሉበት ድረስ ይጓዛሉ፡፡ ሆኖም በፍትህ አካላት ስራ ገብተን ውሳኔዎችን የማስቀልበስ ስልጣን የለንም፡፡ በወልዲያው ችግር ወቅትም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የደረሰበት  ውሳኔ ላይ ተቃውሞ አቅርበናል፤ ግልጽነት ያልነበረው አሰራር እንዳልሆነ አሳውቀን ፌዴሬሽኑ አስነስቶታል፡፡ በአሁኑ ጊዜም እንደ አዲስ የተዋቀረ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አለ፤ የወልዋሎ ቡድንም ይግባኝ ሲያቀርብና ቅጣቱ ሲነሳ ግልጽነት ያለበት ሆኖ እንዲቀርብ እንፈልጋለን፡፡ ሁሉም ክለቦች ለእኛ እኩል በመሆናቸው ከክለቦች ይልቅ ድርጊቱን ነው በጥፋት ደረጃ የምንቃወመው፡፡ ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው እና ክለቦቹም እውነተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ይግባኝ ሰሚው አካል የቅጣት ማሻሻያ ውሳኔዎችን ሲወስን ግልጽ በሆነ መንገድ ”  ቅጣቱ የተነሳላቸው በዚህ አግባብ ነው ፡፡” ማለት ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ክለቦች ትክክል ያልሆነ ሪፖርት ቀርቦላቸው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው በተጨባጭ ከደረሰበት የእርምት እርምጃው በሪፖርት አቅራቢዎቹ ላይ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ቅሬታ ስንጽፍ የሙያተኞቻችን ሪፖርት አቀራረብ ላይ በድሮው ዳኛ፣ ኮሚሽነርና ታዛቢ ተብሎ የሚቀርበው አሁን የውድድር አመራር ተብሎ ይቀየራል፡፡ ስለዚህ ግልጽነት ያለው ውሳኔ ክለቦችን፣ ዳኞችንና ሌሎች አካላትንም የሚጠቅም ነው፡፡፡ የዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር “ቅጣቶች በደፈናው ሊነሱ አይገባም፡፡”የሚል ሀሳብ ነው ያለው፡፡ ቅሬታውን ስናቀርብ የራሳችንም ችግር መታየት ይኖርበታል እንላለን፡፡ የሁለቱ ክለቦች ጉዳይ በሚዲያ ስለቀረበ ነው እንጂ ከዚያም በላይ የሆኑ ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ዋናው ነገር “ወልዲያ አጥፍቷል፤ ወልዋሎም አጥፍቷል፡፡ ሌላውም አጥፍቷል” የሚለው አይደለም፤ ጥፋቶችማ እኮ በሪፖርት ላይ ይቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ በወልዲያ ደጋፊዎች ቅሬታ የለንም፤ እንደውም ለኛ ሲከላከሉ ነበር፡፡ ሆኖም ወደ ሜዳ ውስጥ ገብተው የውድድር አካላት ላይ ችግር በፈጠሩትና ጸብ አንስተው ለዚያ ሁሉ ችግር መንስዔ በሆኑት ዘንድ በተወሰደው ውሳኔ “ቅጣቱ ያንሳል” የሚል ተቃውሞ ነበረን፡፡ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የወሰነው በመሆኑ ምንም አላደረግንም፡፡ አሁንም የቀረበው ሪፖርት ከመጀመሪያው ጀምሮ አግባብነት ሊኖረውም ላይኖረው ይችል ይሆናል፤ ግልጽነት ካለ ክለቦችን ነጻ ያወጣል፡፡ ስለዚህ ቅሬታውን ያቀረብነው ከዚህ አንጻር ነው፡፡ 


“በውድድር አመራሮች የሚቀርበው ሪፖርት ትክክል የመሆኑና ያለመሆኑን ጉዳይ ታይቶ እነዚህ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ ይወሰድ፡፡” የሚል ሐሳብ አለ፡፡ ለዲሲፕሊንም ሆነ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔዎች ደግሞ የውድድር አመራሮች የሚያቀርቡት ሪፖርት ነው እንደ ማስረጃ የሚታየው፡፡ ለምሳሌ የጨዋታ ኮሚሽነሮች ሪፖርት የማቅረብ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዛው ልክ ደግሞ የሪፖርት አቅራቢዎቹን ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል? ይህኛው ትክክለኛ ሪፖርት ነው/ አይደለም ለማለት የሚያስችል መመሪያና ደንብስ አለ?


★ በዚህ ዙሪያ ያለውን አሰራር ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ከሚቀርቡለት ሪፖርቶችና ሌሎች አካላትን ጠይቆ ከሚያገኘው ማስረጃ አንጸር በተለያየ መንገድ ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ የይግባኝ ሰሚው አሰራር ስላልሆነ እና ብዙም የማውቀው ነገር ስለሌለ ኮሚቴው በሚያደርገው ማጣራት ነገሮች ሁሉ ግልጽ ሲሆኑ ነጻ የሚሆኑ አካላት ይኖራሉ፡፡ የክለቦች አለበለዚያም የእኛ ቅሬታ አቅራቢዎች ትክክለኛነት ፍንትው ብሎ ሊታይ ይችላል፡፡ መቼም በህግ ጉዳይ ሀሰተኛ ነገር ሲቀርብ በማጣራት ሒደት ውስጥ መልሶ መላልሶ የመጠየቅ ስርዓት አለ፡፡ ክለቦችም ክስ ይመሰርቱና ይከራከራሉ፡፡ስለዚህ በዚህ መንገድ ሊደረስበት ይችላል፡፡ እኛ ቅሬታችን “ቁልጭ ያለ ነገር መውጣት አለበት፡፡” የሚል ነው፡፡ የተብራራና ግልጽ የሆነ ደንብና መመሪያ ሊኖር ይገባል፡፡ “ክለቦች ጥፋተኛ ያልሆኑበት ምክንያት ተዘርዝሮ ይቅረብ፡፡” የሚል ነው፡፡ 


በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የውሳኔ ማሻሻያ ዙሪያ ባቀረባችሁት ቅሬታ ላይ ተገቢውን ምላሽ ካላገኛችሁ ቀጣይ እርምጃችሁ የሚሆነው ምንድን ነው?


★ በቀጣይነት በእቅድ ደረጃ ያሰብነው የራሳችንን አቅጣጫ ወደ ማየቱ ነው፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ያው <ካስ> ነው፡፡ ነገር ግን “ሁሉንም ሊጠቅሙና ነጻ ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶች ይታዩ፡፡” የሚለው ዋና ነገር ነው፡፡ “ነገሮች እየሄዱ ያሉት ህጋዊ በሆነ መንገድ ነው ወይስ አይደለም?” የሚለውን በደንብ ለመገንዘብ እንሞክራለን፡፡ ክለቦችም እኮ “የተወሰነብን ቅጣት ልክ አይደለም፡፡” ብለው እስከ <ካስ> ድረስ መጓዝ ይችላሉ፡፡ እኛ ግልጽነት የሌለው ነገር በመውጣቱ ‘ቅሬታ ተሰምቶናል!’ ብለን መግለጫ ስናወጣ ቅሬታ መሰማት የለበትም፡፡ ባለፈውም ችግር ያቀረብነው ቅሬታ ነው፤ አሁንም ያው ነው፡፡ አብረን ማስተካከል የሚኖርብን ነገር ካለም ዝግጁ ነን፡፡ እውነት ለመናገር የፌዴሬሽኑ ሐሳብ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌላ ነገር ያተኮረና በመሯሯጥ ላይ ስለሆነ አጽንኦት ሰጥቶ የሚያየው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ቅሬታችንን ማቅረባችን እንደ ጥፋት መታየት የለበትም፡፡ አሁን እንዲያውም መመስገን ያለብን ይመስለኛል፤ “ወደ ራሳችንም እንይ!” እያልን ስለሆነ፡፡ እኛ ጋር ያሉ የጨዋታ አመራሮች ከመጀመሪያ ጀምሮ በክለቦች ላይ በደል የፈጸሙ ከሆነ “ውሳኔ ይተላለፍባቸው!” እያልን ነው ያለነው፡፡ 

ከውይይቶቹ እና ከድርድሮቹ በኋላ ጨዋታዎች መካሄድ ጀምረዋል፡፡ ከዳኞች ጋር በተገናኘ ከሚሰጣቸው ክብር እና እንዲሟሉላችሁ ላቀረባችሁት ጥያቄዎች ከተሰጠው ምላሽ አንጸር  የታዩት ለውጦች ምንድን ናቸው?


★ እኛ እንደ ስራ አስፈጻሚ ሁለት ጊዜ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው በወሰነው መሰረትም ለሶስት ሳምንት ላለመዳኘት ወስነን ነበር፡፡ በአጋጣሚ አዳማ ላይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርታዊ ጨዋነት ምክክር ነበረው፡፡፣ የዳኞችና ታዛቢዎች ማህበርና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በጋራ ሆነን በመነጋገር፣ አቅጣጫዎችንና ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ውይይትና ድርድር አደረግን፡፡ በነገራችን ላይ በቅድመ ሁኔታ ደረጃ የቀረቡት አፋጣኝ መፍትሄ የሚሹ እንጂ ችግሮቻችን እነሱ ብቻ አይደሉም፡፡ በአውሮፓ እንደምናየው ለከበባ፣ ድንፋታ እና ሌሎችም የስነ ምግባር ጉድለቶች በግልጽና በዝርዝር የተቀመጠ ህግ መኖር አለበት፡፡ በመሆኑም ደንቡ መሻሻል አለበት የሚል አቋም አለን፡፡ ከዋና ዋና ነገሮች ውስጥ በኢንሹራንስና የህግ ከለላ ዙሪያ ደግሞ ግንቦት 21 አካባቢ የት ደረጃ እንደደረሰ እንጠይቃለን፡፡  ሁኔታውን ተከታትለን የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የሚወስነው ውሳኔ ይኖራል፡፡ ዘንድሮ ለ30 ዳኞች ኢንሹራንስ ይገባና ችግሩ በመጠኑ እንዲቀረፍ ይደረጋል፤ በሚቀጥለው አመት ደግሞ ለጠቅላላ ወደ 461 ለሚደርሱ ዳኞችና ለ160 የጨዋታ ኮሚሽነሮች ኢንሹራንስ ካልተገባ ውድድር እንደማይጀመር በፌዴሬሽኑ የተፈረመበት ማረጋገጫ ተሰጥቶናል፡፡ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ጉዳይ ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ በወልዲያው ጨዋታ የተመታው ዳኛ የህክምና ወጪ ክለቡ እንዲከፍል ፌዴሬሽኑ ወስኗል፡፡ ሆኖም ዳኛው ወደ ውጪ ሄዶ እንዲታከምና ፌዴሬሽኑ ከክለቡ እንዲጠይቅ ተወስኗል፡፡ 100,000 ብር ተጨማሪ እና ለተለያዩ ወጪዎች እንዲሰጠውም ፌዴሬሽኑ ፈቅዶለታል፡፡ በወልዋሎ ጨዋታ በዳኞች ላይ ለደረሰው በደል ደግሞ የህግ አካል እንዲመደብ በሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ለፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ሴቶቹም ከወንዶቹ እኩል ወደ ክፍለ ሀገር በአውሮፕላን እንዲጓዙ ለሚለው ጥያቄም “ዘንድሮ እንኳ ባይሆን በቀጣዩ ጊዜ እንጠብቃለን፤ ካልሆነ ውድድር አናካሂድም፡፡” የሚል አቋም ይዘናል፡፡ ፌዴሬሽኑ የብቃት ማሻሻያ ትምህርትና ስልጠና መስጠት እንዳለበት ላቀረብነው ጥያቄ “በጋራ የምንሰራው ስለሆነ ትምህርቱንና ስልጠናውን እንሰጣለን፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡


ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነበርና ከውሳኔያችሁ በኋላ ከስፖርት ማኅበረሰቡ፤ ከክለብ አመራሮች፣ ከደጋፊዎች፣ ከሚዲያ አባላትና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ዘንድ የታየው ሁኔታ ምን ይመስላል?


★ አብዛኛዎቹን የሚዲያ አካላት ችግሮችን ግልጽ አድርገው በማውጣታቸው እናመሰግናለን፡፡ በእርግጥ ጨዋታዎችን ማጫወት ስናቆም እንደ “አድማ” ታስቦና ተነግሮ ነበር፡፡ ግን አድማ አልነበረም፡፡ ሁሉም ቆሞ እንዲያስብ ነው ያደረግነው፡፡ በስታዲየሞች ጋዜጠኞች ይሰደባሉ፤ የእንግዳ ቡድን ደጋፊዎች ጫና ይደርስባቸዋል፤ የክብር እንግዶች ሳይቀር ይዘለፋሉ፡፡ስለዚህ የእኛ ጨዋታ መምራትን ማቆም ከለላነቱ ለእኛ ብቻ አልነበረም፤ ይልቅም ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ነበር፡፡ መንግስትም በዚህ ጉዳይ ጥሩ አቅጣጫ እንዲያዝ አድርጓል፡፡ ግልጹን ለመናገር በእግርኳስ ፌዴሬሽናችን ውስጥ የማይደረግ ነገር የለም፡፡ በሀገራችን ኮማንድ ፖስት ሲመሰረት ለደህንነታችን ተብሎ ነው፡፡ እንደ ማስፈራሪያ ሊታይም የሚገባው አይደለም፡፡ የኮማንድ ፖስት ህግ እንደ ተጣሰ ተደርጎ ብዙ ሲባል ነበር፡፡ ፌዴሬሽናችን እኮ ዳኛ ለመመደብ በኮማንድ ፖስቱ ህግ አዋቅሮ በአቶ ጁነዲን ባሻ እንዲመራ ሊደረግ ሲል የዳኞች ኮሚቴ ተከራክሮ ነው ወደ ትክክለኛው መስመር የመጣው፡፡ በነገራችን ላይ የዳኛን ብሄራዊ ኮሚቴን ማንም የሚነካው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኮሊና የአለም አቀፍ ዳኞች ፕሬዘዳንት ነው፤ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጣልቃ ገብቶ ኮሊናን አያዝም፡፡ አቶ ጁነይዲም በብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ውስጥ ገብቶ የማዘዝ ስልጣን የለውም፡፡ የሙያ ማኅበር በሙያተኞች ብቻ ነው የሚመራው፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ ሊዘበራረቁ የደረሱ ነገሮች ነበሩ፤ ያ አሁን ያከተመ ነገር ሆኗል፡፡ ይህን ስል ፌዴሬሽኑ አልሰራም ለማለት አይደለም፡፡ የአስተዳደርና የአመዳደብ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ጥሩ ጥሩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በህክምና፣ በማርኬቲንግ እና ዳኞችን በብዛት በማፍራት ረገድ በበጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኛ ዳኞችም በግል የብቃት ማሻሻል ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ውድድር ብቻ መቁጠር የለብንም፤ ምደባ የፀበል-ጸዲቅ ነገር አይደለም፤ በችሎታ ላይ የሚመሰረት ነው፡፡ ክለቦች የሚበጅቱት ገንዘብ እንዳይባክን ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ምደባን እንደ ርስት የመውሰድ አዝማሚያ በማሳየት “እሱ አስር ፣ እኔ ዘጠኝ…ተመደብኩ” የሚል ነገር ይነሳል፡፡ ጉዳዩ የቁጥር ሳይሆን የችሎታ ነው፡፡ ጣልቃ ገብነት በነበረበት ሒደት ውስጥ ጨዋታ አቋርጠው የወጡ ዳኞችን ስም ጠቅሼ “ጀግኖች ናቸው!” ያልኩት ህጉን መሰረት ስላደረጉ ነው፡፡ ህጉ “ዋናው መሪ ዳኛው ነው፡፡” ይላል፤ ጨዋታ ማቋረጥም ሆነ ማስጀመር የእሱ ስልጣን ነው፡፡ አንዳንድ የዳኛን ክብር የማይጠብቁና ዳኛው ሲመታ የሚያጫውቱ አሉ፡፡ እኛ ጋር ከሚታዩት ችግሮች አንዱ ይህ ነው፡፡ ይህንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡


በቀጣዩ ሳምንት ከሚደረገው ምርጫ ውጤት ምን ትጠብቃላችሁ? አዲስ ፕሬዘዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚመጣ ከሆነ በምን መልኩ በጋራ ለመስራት አቅዳችኀል?


★ ማንም ይመረጥ ከባለሙያዎች ጋር ለመስራት ተዘጋጅተናል፡፡ ባለሙያ ሁሌም በስራው ቦታ ይኖራል፡፡ በምርጫ ወቅት ብዙ ጊዜ ሰው በትኩረት የሚያየው ፕሬዘዳንቱን ነው፡፡ በእርግጥ እሱ መሪ ነው፤ ዋናው ጥንካሬ መኖር ያለበት ግን በስራ አስፈጻሚው ካቢኔ ላይ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ጠንክሮ እንዲሰራ እንፈልጋለን፡፡ ውሳኔዎች የማይቀለበሱና የጸኑ እንዲሆኑ እንሻለን፡፡ ከፖለቲካዊ አመለካከት የጸዳ አመራር እና የስፖርት ማኅበረሰብ ልንሆን ይገባል፡፡ ስልጣኑ የዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ እስከሆነ ድረስ ለክለቦች “ይህ ዳኛ አይመደብብኝ!” የሚል መብት መሰጠት የለበትም፡፡ በውድድሮች ላይ በሚፈጠሩ  ችግሮች ውሳኔዎች ሲወሰኑ የግለሰቦች ጣልቃ ገብነት ነገሮችን ሲያበላሽ አስተውለናል፡፡ እነዚህ ነገሮች መስተካከል አለባቸው፡፡ ተመራጮቹ አመራሮች ወደ ቦታው እንደመጡ በየፊናው ባሉት ችግሮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ሰዎች ጋር ንግግር ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ “እኔ የእገሌ ደጋፊ ነኝ፡፡” በሚል ካሁኑ በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ቦታ ለማግኘት ያሰፈሰፉ ሰዎች አሉ፡፡ ሆኖም ድርጊቱ ምንም አያዋጣንም፤ ሁላችንንም የሚጎዳ ሒደት ነው የሚፈጥረው፡፡ ጠንካራና ለሙያቸው ያደሩ ሰዎችንም እየተመለከትን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለጠቅላላ ጉባዔው ማስተላለፍ የምፈልገው በሙያው ውስጥ ያለፉና ጠንክረው የሚሰሩ ስራ አስፈጻሚዎችን እንዲመርጥ ነው፡፡ ደጋግሜ እንደምናገረው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያሉትን ነው እኔም የማስቀምጠው “ስንደመር ኢትዮጵያዊ ነን፡፡” በየክልሉ ብንሄድ የአንድ ክልል ብቻ የሆነ ስፖርተኛ አናገኝም፤ እንዲያውም በየቦታው በኢትዮጵያዊነት ስሜት የተሰባጠረ ስብስብ ነው የምናየው፡፡ እኛ ዳኞች ጋር ብንመጣ እንኳ ከአንድ ዘር ብቻ የሆነ የለም፡፡ ከጠቅላላው ብሔር እና ህዝብ የተደባለቀ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በስፖርቱ ዘርፍ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከዚህ አስተሳሰብና መውጣት አለበት፡፡ ስፖርት ከፖለቲካም ሆነ ከሃይማኖት ነጻ ነው፡፡ እኔ በተለያዩ የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብና ሌሎች ክልሎችም እየሄድኩ አጫውታለሁ፤ አንድም ቀን በብሄር ጉዳይ ተሰድቤ አላውቅም፡፡ ራሳችን በተለይ ደግሞ ክለቦች፣ ዳኛ፣ አሰልጣኝና ተጫዋቾች “እኔ ከዚህኛው ብሄር ስለሆንኩ… እኔ ደግሞ ከዚያኛው ዘር ስለሆንኩ…” እያሉ የሚሰጡት አስተያየት አደጋ ስላለው መልሶ ችግር ይዞብን እንዳይመጣ መጠንቀቅ አለብን፡፡ አስፍተን እንደ አገር ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡ እኛ ዳኞችና ኮሚሽነሮች ጋር ችግሮችን ከደጋፊዎች፣ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ የክለብ አመራሮችና ፌዴሬሽኑ ጋር የማያያዝ ብቻ ሳይሆን ካጠፋን ደግሞ ራሳችን ላይ እርምት ለመውሰድ መዘጋጀት አለብን፡፡ አንድ ልናገር የምፈልገው ደግሞ እኛ ክለቦች ይጎዱ የሚል አመለካከት የለንም፤ ሁሉም ክለቦች ለእኛ እኩል ናቸው፡፡ አንድን ነገር ስለተቃወምንና ቅሬታ ስላቀረብን ወደ አንድ ነገር በሚያጋድል አስተያየት መፈረጅ የለብንም፡፡ ሁሌም የሚነሳውን የሪፖርት ተዓማኒነት ጥያቄ መፍትሄ ለመስጠትና ክለቦችንም እኛንም ስለሚጠቅም ውሳኔዎች ማሻሻያ ሲደረግባቸው “ግልጽነት ባለውና ዘርዘር ባለ ሁኔታ ይቅረብ፡፡” የምንለው፡፡ አንዳንድ ክለቦች በዚህ ደስተኛ ስላልሆኑ “ለምን ይቃወሙናል?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ስለተቃወምን ብቻ ግን ትክክል ነን ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን ነገር ለማወቅ ግልጽ የሆነ ነገር ይኑረን፡፡ 


ያለፈው የሚያዝያ ወር ዳኞች ክብር እንዲያገኙ ያስቻለና ችግሮቻቸው ጎልተው የታዩበት ጊዜ ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ የተለመደው እንዲህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ “ሰሞነኛ” የሆኑ መፍትሄዎች ያገኙና በቀላሉ ያልፋሉ፡፡ ይህንን ለመቅረፍና በዘለቄታዊነት ችግሩን ለማስወገድ ምን እየሰራችሁ ነው? ለሚቀጥለው የወድድር ዘመን እንዲካተት የምትፈልጉት ህግና ደንቦች በምን መልኩ እንዲረቁ ግፊት እያደረጋችሁ ነው? ህብረተሰቡ በዳኝነት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግስ ምን ለመስራት አስባችኋል?


★ እኛ በፊፋ መመዘኛ መስፈርት መሰረት ዳኞቻችንን የምንገመግምበት ሒደት አለን፡፡ ዳኞች በየጨዋታው ከሚጠበቅባቸው መስፈርት በታች ሲያመጡ ይቀጣሉ፡፡ እኛ ጋር ያለውን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ትልቅ ውይይት አድርገን ለማስተካከል አቅደናል፡፡ በውይይቱ ከጠቅላላ ጉባኤው በተጨማሪ ከዳኞችና ታዛቢዎች ለሚወጡት ህጎች ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን የመውሰድ እቅድ አለን፡፡ በፌዴሬሽኑ በኩል ደግሞ ህጉ መጥበቅ አለበት፡፡ህጉን ለማስተካከል ጫና መፍጠር ያለብን እኛ ብቻ ሳንሆን ሁላችንም እግርኳሱ የሚመለከተው ሁሉ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ስናጸድቀውም ለግላችን ብለን እንዳልሆነ ሊታሰብ ይገባል፡፡ ውይይቶች ሲደረጉም ሁሉንም ክለቦች ያማከለና ያሳተፈ እንጂ የተወሰኑት ብቻ ተመርጠው ጠቅላይና ወካይ አድርጎ መሆን የለበትም፡፡ ለእኛ ክለቦችም ሆኑ የሚዲያ አካላት ጥሩ ናቸው፡፡ አበል ስንጠይቅ እኮ ክለቦች ፈቅደው ነው ጭማሪ የተደረገልን፡፡ አብዛኛዎቹ በጨዋነት ሁሌም የሚተባበሩን ክለቦች አሉ፤ ሊከበሩ ይገባቸዋል፤ እናመሰግናቸዋለንም፡፡