ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ደደቢት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ይገናኛሉ። ተጠባቂውን ጨዋታ በቅደመ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ቃኝተነዋል። 

ከዛሬ በኃላ ስድስት ጨዋታዎች ብቻ በሚቀሩት የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ የሆኑት ክለቦች ቀስ በቀስ እየተለዩ ነው። ዛሬ የመዲናዋን ክለቦችን በሚያገናኘው ጨዋታ ደግሞ ሽንፈት ክለቦቹን በተለይ ደግሞ ደደቢትን ሙሉ ለሙሉ ከፉክክሩ የሚያርቅ ነው። ከአንደኛው ዙር እጅግ ተቃራኒ የሆነ የቁልቁለት ጉዞውን የተያያዘው ደደቢት በሁለተኛው ዙር ከአራት ነጥቦች በላይ መሰብሰብ አልቻለም። ይህ ውጤቱም ሊጉን ከመምራት ወርዶ ስድስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ቡድኑ በሰባት ጨዋታዎች አንድ ጎል እንኳን ማስቆጠር ከብዶት ከየካቲት ወር በኃላ በአንድ ጨዋታ ሶስት ጎል ያገኘበት የሳምንቱ ጨዋታም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 4-3 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር። ደደቢት ከዛሬው ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ካልቻለ በዘንድሮው ውድድር  ከመሀል ሰፋሪ ቡድኖች ተርታ ለመመደብ የሚገደድ ይመስላል። 

ዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች ተርተ ለመመደብ ጫፍ እየደረሰ መልሶ የሚንሸራተተው ኢትዮጵያ ቡና 36 ነጥቦችን ይዞ ይገኛል። 40ን የተሻገሩት ከበላዩ ያሉትን ሶስት ክለቦች በቅርበት ለመከተል ዛሬ ደደቢትን የመርታት ግዴታ አለበት። ኢትዮጽያ ቡና ከአርባምንጭ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ጋር ካደረጋቸው ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቱ ጎዳው እንጂ በሁለተኛው ዙር በርከት ያሉ ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። ሆኖም ለቡናማዎቹ የሻምፒዮንነት ጉዞ ፈተና የሆነው ከዋንጫ ተፎካካሪ ቡድኖች ጋር በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ተገቢውን ነጥብ አለማግኘት ነው። በዘንድሮው ውድድር ቡድኑ በድል ከተወጣቸው ጨዋታዎች ውስጥ ፋሲል ከተማ ላይ ያስመዘገበው የ3-2 ውጤት በሊጉ ወገብ በላይ የሆነን ቡድን ያሸነፈበት ብቸኛ ጨዋታ ነበር። በመሆኑም የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ቡድን ቀሪ ጨዋታዎቹ የሻምፒዮንነት ፉክክር ጣዕም እንዲኖራቸው ዛሬ አሸናፊ መሆን ይጠበቅበታል። 

ተጠባቂ በሆነው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጉዳት የማይሰለፈው የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አጥቂ አስቻለው ግርማ ብቻ ሲሆን ለአስናቀ ሞገስ ደግሞ ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ በተመለከትው ቀይ ካርድ የመጨረሻ የቅጣት ቀን ይሆናል። በደደቢት በኩል ግን ሽመክት ጉግሳ ከቅጣት ከመመለሱ በቀር ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ብቁ እንደሆነ ታውቋል።

ከቡድኖቹ አጨዋወት ፣ ከውጤቱ አስፈላጊነት እና ከእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪካቸው አንፃር ማጥቃት ላይ የተመሰረተ እና በርካታ ሙከራዎች የሚደረጉበት ጨዋታ ከሁለቱ ቡድኖች ይጠበቃል። የኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት የሚያደርገው ኢትዮጽያ ቡና በዛሬው ጨዋታም የበላይ ለመሆን የአማካይ ክፍሉን ጥንካሬ አብዝቶ ይፈልጋል። ከምንም በላይ ተጋጣሚው ወደ መከላከል ሲሸጋገር በሶስቱ አጥቂዎቹ እና በቀሪዎቹ አማካዮች መሀል የሚተወው ሰፊ ክፍተት ለኢትዮጵያ ቡና የመሀል ክፍል ተሰላፊዎች የእንቅስቃሴ ነፃነትን የሚያስገኝላቸው ነው። በመሆኑም ፍጥነት ባላቸው የጠሩ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል መግባት ከቻሉ ቡናዎች በቁጥር በርክተው የደደቢትን የተከላካይ መስመር የማስጨነቅ እድልን ሊያገኙ ይችላሉ። በዚህ ወቅት ደግሞ ቡድኑ የሜዳውን ስፋት የሚጠቀምበትን መላ ከመስመር ተሰላፊዎቹ ካገኘ ማጥቃቱን የማገዝ ሀላፊነት የተጣለባቸው አማካዮቹ የመጨረሻ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ወደ ሳጥን ውስጥ ለማድረስ የሚቀላቸው ይሆናል።

 አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከቅጣት በተመለሱበት እና የቡድናቸውን የበፊት ቅርፅ በተመለከትንበት የኤሌክትሪኩ ጨዋታ ቢሸነፍም ሶስት ግቦች ማስቆጠሩ በተለይ በማጥቃቱ በኩል ዛሬም ተመሳሳይ አካሄድ ሊኖረው እንደሚችል ይነግረናል። ፊት ላይ ሶስት አጥቂዎችን የሚጠቀመው ደደቢት የኢትዮጵያ ቡናን ግራ እና ቀን የተከላካይ መስመር ዋነኛ የጥቃት ኢላማ እንደሚያደርግ ይገመታል። ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ ሊወሰድ ከሚችልበት ብልጫ አንፃር የመስመር አጥቂዎቹ በማጥቃት ላይ በስፋት ሲሳተፉ የሚታዩት የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዮሽን የማፈን ሀላፊነት ቢኖርባቸውም ቡድኑ ወደ ማጥቃት በሚሸጋገርባቸው ወቅቶች ግን ሁለቱን ኮሪደሮች በአግባቡ የመጠቀም ግዴታ አለባቸው። የደደቢት የማጥቃት አማካዮች ወደ አስራት መገርሳ ተገፍተው ለመንቀሳቀስ መገደዳቸው የሚቀር ስለማይመስልም በብዛት ሲያደርገው እንደታየው ጌታነህ ከበደ በጥልቀት ወደኃላ እየተሳበ ኳሶችን ተቀብሎ ለሽመክት እና አቤል ያለው ማድረስ ከቻለ ነገሮች ለኢትዮጵያ ቡና የኃላ ክፍል ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከላይ ከተነሱት ነጥቦች ውጪ ደግሞ ትናንት እንደተመለከትነው የአዲስ አበባ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳ በዝናብ የሚጨቀይ ከሆነ ወደ ፊት የሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ልዩነትን የሚፈጥሩበት ዕድል ሰፊ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ጌታነህ ከበደ እና ባፒስታዬ ፋዬ የሚኖራቸው ሚና ተጠባቂ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 17 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ደደቢት 10 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ አሸንፏል። አንድ ጊዜ ብቻ (አምና) አቻ ተለያይተዋል።

– በርካታ ጎሎችን በሚያስተናግደው የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት 53 ጎሎች ሲቆጠሩ ደደቢት 30 ፣ ኢትዮጵያ ቡና 23 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

– በአንድ አጋጣሚ (2009) ላይ ያለ ጎል አቻ ከመለያየታቸው በቀር በሌሎቹ ጨዋታዎች ሁሉ ግቦች ተስተናግደዋል

– በመጀመርያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው (2002 የውድድር ዘመን) ደደቢት 1-0 ያሸነፈ ሲሆን በመጨረሻው ግንኙነታቸው (ዘንድሮ አንደኛው ዙር) በተመሳሳይ ደደቢት 1-0 አሸንፏል። አስገራሚው ነገር በሁለቱም ጨዋታዎች የማሸነፍያ ጎሎች የተቆጠሩት በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ነው።

– ደደቢት ካለፉት 10 ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ አስመዝግቦ እጅግ መጥፎ አቋም ላይ ይገኛል። ባለፉት አራት ተከታታይ ጨዋታዎችም ሽንፈት አስተናግዷል።

– ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ወጣ ገባ አቋም በማሳየት ላይ ይገኛል። (ሽንፈት-ድል-ሽንፈት-አቻ-ድል)

ዳኛ

– ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንዲመራ የተመደበው ፌደራል ዳኛ ማኑኤ ወልደፃዲቅ ነው።