የ19ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ውሎ…

የ19ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ጨዋታዎች በተለያዩ ከተሞች ሲደረጉ ባህር ዳር ከተማ ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ያሰፋበትን ድል አስመዝግቧል። ሽረ እና አአ ከተማ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

ባህርዳር ከተማ 5-1 ቡራዩ ከተማ

(ሚካኤል ለገሰ)

ባህርዳር ላይ ባህርዳር ከተማ ቡራዩ ከተማን በሜዳው አስተናግዶ በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። ከትላንት በስቲያ በድንገት ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት የደደቢት እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያሳየን ሲሆን ተመልካችንም በግብ አምበሽብሿል።

በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ክፍለ ጊዜያት ተጋባዧቹ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ቶሎ ወደ ጨዋታው ሪትም ያልገቡትን ባህርዳር ከተማዎችን አስጨንቀው የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ታይቷል። በ22ኛው ደቂቃ የቡራዩ የአጥቂ መስመር ተጨዋች ኢሳይያስ ታደሰ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮት ወደ ግብ ቢሞክራትም ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ተቆጣጠራት እንጂ ገና በጊዜ ጎል የምናይበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።

በ39ኛው ደቂቃ የቡራዩ የመስመር ተጫዋች ኳሷን ወደ ግብ ሲያሻማት የባህርዳር የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ወንድሜነህ ደረጄ ኳሷን አወጣለው ብሎ ተጨርፎበት የመጀመሪያ ግብ ቡራዩዎች ቢያገኙም መሪነታቸውን ግን ከአንድ ደቂቃ በላይ ማስጠበቅ አልቻሉም። በ40ኛው ደቂቃ የቡራዩ ተጨዋቾች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት በመስራታቸው የተገኘው የፍፁም ቅጣት ምትን ፍቃዱ ወርቁ በአግባቡ በመጠቀም ባህርዳርን አቻ ማድረግ ችሎ የመጀመርያው አጋማሽ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተደጋጋሚ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን በተወሰኑ የደቂቃ ልዩነቶች ውስጥ ሲያደርጉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ መሪ መሆን የሚችሉበት ጎል ማግኘት የቻሉት ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ8 ደቂቃ ውስጥ ነበር። ፍቃዱ ወርቁ ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል በማግባት በስታዲየሙ የሚገኙ ደጋፊዎችንም ማረጋጋት ችሏል። ተጋባዦቹ በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተዳክመው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በተለይ ግብ ጠባቂው አሸብር ደምሴ እና የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ከፍተኛ የትኩረት ማጣት ችግር እንደነበረባቸው በግልፅ ለማየት ተችሏል። በ71ኛው ደቂቃ የመሃል መስመር ተጨዋቹ ዳንኤል ኃይሉ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ የመታት ኳስ ወደ ግብነት ተቀይራ ሶስተኛ ሆና ተመዝግባለች። በ79ኛው እና በ87ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጨዋቹ ሙሉቀን ታሪኩ ሁለት ግቦችን አከታትሎ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ አምስት ማሳደግ የቻለ ሲሆን በተለይ መጀመሪያ ያስቆጠራት ግብ የተጫዋቹን ድንቅ ብቃት የምታሳይ ነበረች። ጨዋታው በዚህ መልኩ መጠናቀቁን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 41 በማድረስ ከተከታዮቹ በ6 ነጥቦች ርቆ መምራቱን ቀጥሏል።

ሽረ እንዳስላሴ 1-1 አዲስ አበባ ከተማ

(ማትያስ ኃይለማርያም)

ባህርዳር ከተማን እየተከተሉ የሚገኙት ሽረ እንዳስላሴ እና አዲስ አበባ ከተማ ያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በቻ ውጤት ተጠናቋል። ሽረ እንዳስላሴ ያጋጠመው የበጀት እጥረትን ለመቅረፍ በማሰብ ከሽረ ወደ መቐለው ትግራይ ስታድየም የተዘዋወረው ይህ ጨዋታ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ግብ በመድረስ እንግዶቹ አአ ከተሞች ተሽለው የታዩ ሲሆን በ4ኛው ደቂቃ ላይ ናይጄርያዊው ግዙፉ አጥቂ ላኪ ሳኒ ከመስመር የተላከችለት ኳስ በግንባሩ በመግጨት እንግዶቹ መሪ ማድረግ ችሏል።

አአ ከተማዎች ጠቅጠቅ ብለው ብለው በመከላከል እንዲሁም እንደ ቡድን በማጥቃት ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም እንደወሰዱት ብልጫ የጠሩ የጎል እድሎች መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በ24ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ዓለሙ በግል ጥረቱ ያገኛትን ኳስ አክርሮ ቢመታም ተከላካዮቹ ተደርበው ያወጡበት ኳስ የምትጠቀስ ነበረች። ቀስ በቀስ የተወሰደባቸው የጨዋታ ብልጫን በማስመለስ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ሽረዎች በፍጥነቱ እጅግ የተቀዛቀዘ የማጥቃት ሽግግር በመምረጣቸው እና ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች በተወሰኑ ተጫዋቾች ለመጠቀም በመሞከሩ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ከገባ በኋላ በቁጥር ለመበለጥ ተገደዋል። ልደቱ ለማ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት የጎሉን ብረት ታካ የወጣችው እና ከቅጣት ምት የተሻገረለት ኳስ አግኝቶ ያመከናት በሽረ በኩል የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ። በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሽረዎች በ39ኛው ደቂቃ ላይ የ ፍ.ቅ.ም ቢያገኙም ልደቱ ለማ ሳይጠቀምባት ቀርቷል። በአአ ከተማ በኩልም በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ ተነክታለች በሚል ፍ.ቅ.ም ይገባናል ቢሉም የእለቱ ዳኛ በዝምታ አልፈውታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ የነበራቸው ብርቱ ፍላጎት ተከትሎ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ፍሰት ቢያሳዩም በሙከራ የታጀበ አልነበረም። የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ የሽረው ልደቱ ለማ በግል ጥረቱ ተጫዋቾች አልፎ ቢመታውም ፍሬው ጌታሁን በጥሩ ብቃት ጎል ከመሆም አግዷታል። በ56ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ዘላለም ታሪኩ በመጀመርያ የኳስ ንክኪው በቅጣት ምት ሽረን አቻ ማድረግ ችሏል። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር አአ ከተማ ለአጥቂዎቹ በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች በመጠቀም ሁለት ያለቀላቸው እድሎች ቢያገኙም መጠቀም አልቻሉም። በተለይ በጨዋታው ኮኮብ ሆኖ የዋለው ምንያምር ጴጥሮስ ያሻማው ኳስ ላኪ ሳኒ በግንባሩ ቢገጭም የግቡ ቋሚ መልሶበታል። ከዚ ውጭ ከመጀመርያው ጎል በተመሳሳይ ላኪ ሳኒ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ቢያስቆጥርም በእለቱ ረዳት ዳኛ ተሽራለች። ምያምር ጴጥሮስ በረጅሙ የተሻገረለት ኳስ እየገፋ ሄዶ ከግብ ጠባቂው ቢገናኝም በሙሴ ዮሃንስ ጎል ከመሆን የተረፈችው አጋጣሚም የአአ ከተማ ሌላው ሙከራ ነበር።

ሌሎች ጨዋታዎች

አውስኮድ ከአክሱም ከተማ መድን ሜዳ ላይ ያደረጉት ጨዋታ በአክሱም ከተማ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሽመክት ግርማ የብቸኛዋ ጎል ባለቤት ነው። ኢኮስኮም ፌዴራል ፖሊስን አስተናግዶ በተመሳሳይ 1-0 ሲያሸንፍ ይበልጣል ሽባባው የማሸነፍያዋን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል። ነቀምት ከተማ ደሴ ከተማን 2-0 አሸንፏል። ገዛኸኝ ባልጉዳ ከእረፍት በፊት እንዲሁም ብሩክ ብርሀኑ በሁለተኛው አጋማሽ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

በዘንድሮው የውድድር አመት በርካታ የአቻ ውጤት እያስተናገደ ያለው ኢትዮጽያ መድን ከሰበታ ጋር 2-2 አቻ ተለያይቷል። ለመድን ሀብታሙ መንገሻ እና ታምራት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ለሰበታ ዳንኤል ታደሰ እና ጌቱ ኃይለማርያም አስቆጥረዋል። በዝናብ የተቋረጠው የየካ እና ወሎ ኮምበልቻን ጨዋታ ዛሬ ቀጥሎ ሲካሄድ 1-1 ተጠናቋል። ጨዋታው ከመቋረጡ በፊት በ57ኛው ደቂቃ አንተነህ ተሻገር ወሎ ኮምቦልቻን ቀዳሚ ቢያድርግም የካዎች ዛሬ ላይ በቀጠለው ጨዋታ ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። ሱልልታ ከ ለገጣፎ ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ የምድቡ ብቸኛ ጨዋታ ነው።