ጋና 2018 | ሉሲዎቹ ዛሬ ምሽት አልጄርያን ይገጥማሉ

በጋና አስተናጋጅነት በ2018 መጨረሻ የሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ የማጣርያ ዙር የሚቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት ከአልጄርያ ጋር የመጀመርያ ጨዋታውን ያደርጋል።

የሊብያ ሴቶች ቡድንን 15-0 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፈው ወደመጨረሻው ዙር ያለፉት ሉሲዎቹ በግብፅ በኩል አድካሚ ጉዞ አድርገው ወደ አልጄርያ ያመሩ ሲሆን ለጨዋታው የሚያደርጉትን ዝግጅትም በስፍራው ቀጥለዋል።

የቡድኑ አሰልጣኝ የሆነችው ሰላም ዘርዓይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠችው አስተያየት ስለ ቡድኑ ዝግጅት ይህን ብላለች።

“ዝግጅታችን ጥሩ ነው፤ ሁሉ ነገርም ጥሩ ነው። ሜዳ  ላይ ሊፈጠሩ ከሚችሉ ነገሮች ውጭ በሚቻለን አቅም ሁሉ ለመጫወት ጥረት እናደርጋለን። ከመጀመሪያው ቀን እንግልት ውጭ ለ11 ሰዓታት ከግብፅ ወደ አልጄሪያ ለመምጣት ረጅም ትራንዚት ተጉዘን ነበር የደረስነው። ከደረስን በኋላ ድካም ስለነበረብን የግብፅ የታዳጊዎች ቡድን ከአልጄሪያ ያደረገውን ጨዋታ በመመልከት ነው ያሳለፈነው። ከሁለተኛው ቀን ጀምረን ግን ጨዋታውን በምናደርግበት የምሽት ሰዓት ላይ ተከታታይ ልምምዶችን ሰርተናል። ተጋጣሚያችንም ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡት በየሚዲያዎቻቸው እየተመለከትኩ ነው። በሜዳ ላይ ያለውን ሒደት አብርን የምናየው ይሆናል፡፡”

ኢትዮጵያ እና አልጄርያ በ2016 የካሜሩን የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ በመጀመርያ ዙር ማጣርያ መገናኘታቸው የሚታወስ ሲሆን አልጄርያ በድምር ውጤት 2-1 አሸንፋ ቀጣዩ የማጣርያ ዙር ማለፏ የሚታወስ ነው።

በአልጀርሱ ጁላይ 5 ስታድየም ምሽት 05:30 ላይ የሚካሄደውን ይህን ጨዋታ ጋምቢያዊቷ ኢሳቱ ቱሬ በመሐል ዳኝነት ስትመራው የሀገሯ ዜጎች የሆኑት አቢ ሌሲይ እና ጃይነባ ማኔህ በረዳትነት ተመድበዋል።
የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታ ተጋጣሚዎች

ሌሶቶ ከ ደቡብ አፍሪካ

ዛምቢያ ከ ዚምባብዌ

ኮንጎ ሪፐ. ከ ካሜሩን

ጋምቢያ ከ ናይጄርያ

አይቮሪኮስት ከ ማሊ

ኬንያ ከ ኢኳቶሪያል ጊኒ

አልጄርያ ከ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ እና አልጄርያ የመልስ ጨዋታ እሁድ ሰኔ 3 በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋል። ያሸነፈው ቡድንም በቀጥታ ወደ ጋናው የአፍሪካ ዋንጫ ያልፋል።