የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዲቪዝዮን 25ኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዲቪዝዮን 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከረቡዕ ጀምሮ እስከ ትላንት ተካሂደው ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን የሚሸጋገር አንድ ተጨማሪ ቡድን እና ለላኛውን በእጅጉ ያስጠጋ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የሊጉ ቻምፒዮን መሆኑን ባለፈው ሳምንት ያረጋገጠው ጥረት ኮርፖሬት ረቡዕ ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ ግርጌ ላይ የሚገኘው ንፋስ ስልክ ላፍቶን 4-0 አሸንፏል። ምስር ኢብራሂም ሁለት ጎሎችን ስታስቆጥር ሊድያ ጌትነት እና ነፃነት ሰውአገኝ ሌሎቹን ግቦች አስቆጥረዋል። ጥረት ነጥቡን ወደ 63 ከፍ ማድረግም ችሏል። ቀጥሎ በዛው በአዲስ አበባ ስታድየም በተካሄደው ጨዋታ ጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች አካዳሚ ቦሌ ክፍለ ከተማን 2-1 በማሸነፍ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ለመግባት በእጅጉ መቃረብ ችሏል። የጥሩነሽን ወሳኝ ጎሎች ያስቆጠሩት ጤናዬ ላታሞ እና ትንሳኤ ሸቡ ናቸው። ጥሩነሽ በድሉ ተጠቅሞ ነጥቡን 44 ሲያደርስ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ለመቀላቀል ከመጨረሻው ጨዋታ አንድ ነጥብ መያዝ ይበቃዋል።

ሀሙስ በ8:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በቂርቆስ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሰላም ለገሰ፣ ትግስት ኃይሉ እና ጋብሬላ አበበ የአሸናፊው ቡድን ጎል አስቆጣሪዎች ናቸው። አዲስ አበባ ከተማ ሽንፈት ቢያስተናግድም ተከታዮቹ ቡድኖች ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን የተሸጋገረ 3ኛው ክለብ መሆን ችሏል። በመቀጥል 10:00 ላይ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ለማለፍ የተሻለ እድል የነበረው ኢትዮጽያ ቡናን ከሌላው የማለፍ እድሉ ካልተሟጠጠው ልደታ ክፍለ ከተማ ያገናኘውን ጨዋታ ልደታ በለምለም ወልዱ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል። ውጤቱን ተከትሎም ሁለቱም በእኩል 41 ነጥብ እጅግ በጣም ዝቅተኛ የማደግ ተስፋን ይዘው ወደ 26ኛ ሳምንት ተሸጋግረዋል። በክልል ከተማ በተካሄደ የሳምንቱ ብቸኛ ጨዋታ ሳሸመኔ ላይ ፋሲል ከተማ ሻሸመኔ ከተማን 2-1 ማሸነፍ ችሏል።

አርብ 08:00 ላይ ቅደስት ማርያም እና አስቀድሞ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ማደጉን ያረጋገጠው አርባምንጭ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። 10፡00 ላይ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወጣቶች አካዳሚን 1-0 አሸንፏል። በአንደኛ ዲቪዝዮን የመሳተፍ አላማ እንደሌለው የተገለፀው አካዳሚ በዚህ እና ቀጣይ ጨዋታዎች ድል ቢያስመዘግብ የማደግ እድል ነበረው።
የሳምንቱ ጨዋታዎችን ተከትሎ የደረጃ ሰንጠረዡ እንዲህ ሆኗል

በ2011 ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ማለፋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች

1 ጥረት ኮርፖሬት (ቻምፒዮን)

2 አርባምንጭ ከተማ

3 አዲስ አበባ ከተማ

* ቀሪው አንድ ቡድን በቀጣዩ ሳምንት በሚደረጉ ጨዋታዎች ይታወቃል። ጥሩነሽ ለማለፍ አንድ ነጥብ ሲበቃው ቡና እና ልደታ ለማለፍ በሰፊ ጎል ከማሸነፍ በተጨማሪ የጥሩነሽን በሰፊ ጎል መሸነፍ ይጠብቃሉ።
የመጨረሻ (26ኛ) ሳምንት መርሀ ግብር

ማክሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2010

08:00 ልደታ ከ ቦሌ (አአ)

10:00 ቂርቆስ ከ ንፋስ ስልክ (አአ)

ሀሙስ ሰኔ 14 ቀን 2010

09:00 ኢወስ. አካዳሚ ከ ሻሸመኔ ከተማ (አአ)

እሁድ ሰኔ 17 ቀን 2010

09:00 ጥረት ከ አቃቂ ቃሊቲ (ባህርዳር)

09:00 አርባምንጭ ከ ኢትዮጵያ ቡና (አርባምንጭ)

09:00 ጥሩነሽ ዲባባ ከ አአ ከተማ (አሰላ)

09:00 ፋሲል ከተማ ከ ቅድስት ማርያም ዩ. (ጎንደር)