ኡመድ ኡኩሪ ድንቅ አጀማመር አደረገ

ባለፈው ወር የኢትዮጵያው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ የግብፁን ኢትሃድ – አሌሳንድሪያ የተቀላቀለው ኡመድ ኡኩሪ ለክለቡ የመጀመርያ በሆነው ጨዋታ ግብ አስቆጥሮ ወጥቷል፡፡

በ1914 የተመሰረተው ኢትሃድ አሌሳንድሪያ የተመሰረተበትን 100ኛ አመት ለማክበር ከፖርቱጋሉ ታላቅ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

በአሌሳንድሪያ በ20,000 ተመልካቾች ፊት በተደረገው ጨዋታ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ስፖርቲንጎች በ6ኛው ደቂቃ በጁአኦ ማርዮ አማካኝነት ነው፡፡

በ28ኛው ደቂቃ ኡመድ ኡኩሪ ኢትሃድን አቻ ያደረገች ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በ78ኛው ደቂቃ ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡

በ82ኛው ደቂቃ ስፖርቲንግ ሊዝበን በጁንያ ታናካ ባስቆጠረው ግብ በድጋሚ መምራት ቢችሉም ጨዋታው ተጠናቆ በተጨማሪው ደቂቃ አሊ አፊፊ ግብ አስቆጥሮ ኢትሃድን ከሽንፈት አድኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *