ድሬዳዋ ሲሳይ ደምሴን ሲያስፈርም ወሳኝ ተጫዋቾቹን በተሸሻለ ውል እያስፈረመ ነው

የብሄራዊ ሊጉ ቻምፒዮን ድሬዳዋ ከነማ የ2008 የፕሪሚየር ሊግ ስብስቡን ለማጠናከር ተጫዋች በማስፈረም እና ኮንትራ በማደስ ላይ ይገኛል፡፡

ድሬዳዋ ከነማ ወደ ፕሪሚር ሊጉ ካደገ በኋላ በርካታ ተጫዋቾች ስማቸው ከክለቡ ጋር ሲያያዝ የቆየ ሲሆን ተከላካዩ ሲሳይ ደምሴን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል፡፡

የቀድሞው የኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ በመከላካያ የነበረውን ውል ማጠናቀቁን ተከትሎ ያለፉትን ወራት ክለብ አልባ ሆኖ የቆየ ሲሆን በመጨረሻ ማረፍያውን ድሬዳዋ ከነማ አድርጓል፡፡

ክለቡ ተጫዋች ከማስፈረም በተጨማሪ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በክለቡ ለማቆየት ድርድር እያደረገ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ በክለቡ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ተጫዋች የፈረሙት በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን መጀመርያ በመሆኑ ቀሪ የአንድ አመት ኮንትራት ይቀራቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ቀሪ ኮንትራት ቢኖራቸውም የፕሪሚየር ሊጉ ታላላቅ ክለቦች በከፍተኛ ደሞዝ ተጫዋቾቹን ለማዘዋወር ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ድሬዳዋ የደሞዝ መጠናቸውን ከፍ በማድረግ ለማቆየት ጥረት እደረገ ይገኛል፡፡

የብሄራዊ ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ይሁኔ እንደሻውን ጨምሮ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ድሬዳዋ ከነማ ባቀረበላቸው የደሞዝ ማሻሻያ መስማማታቸው የታወቀ ሲሆን ባላቸው ቀሪ አንድ አመት ኮንትራት የሚከፈላቸው ደሞዝ የ2 አመት ኮንትራት ሲፈርሙ በተስማሙት ሳይሆን በዝውውር መስኮቱ ሌሎች ክለቦች ያቀረቡላቸውን ከፍተኛ ደሞዝ ያማከለ የተሻሻለ የገንዘብ መጠን ነው፡፡

ብሄራዊ ሊጉን በከፍተኛ ግብ አግቢነት ያጠናቀቀው የበላይ አባይነህ ጉዳይ ግን ከሌሎቹ ተጫዋቾች የተለየ ሆኗል፡፡ ተጫዋቹ የድሬዳዋ የአየር ሁኔታ እንዳልተስማማው በመግለፅ ሌሎች አማራጮችን እንደሚመለከት ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡

ቀድሞ የነበረው ክፍያ እንዲሻሻል ጥያቄ ቢያቀርቡልኝም የድሬዳዋ ከፍተኛ ሙቀት ስላልተስማማኝ መልቀቅ ነው የምፈልገው፡፡ ከክለቡ ጋር ከተስማማን ቀሪ አንድ አመት ውሌን በስምምነት አፍርሼ የአየር ንብረቱ ቀዝቀዝ የሚልበት አካባቢ ወዳሉ ክለቦች መሄድ ምርጫዬ ነው፡፡ ክለቡ ጥያቄዬን ካልተቀበለ ግን ያለኝን አንድ አመት ቀሪ ኮንትራት ለማጠናቀቅ እገደዳለሁ፡፡›› ብሏል፡፡

በተያያዘ ዜና ከአድካሚው የብሄራዊ ሊግ መጠናቀቅ በኋላ እረፍት ላይ የሚገኙት የድሬዳዋ ከነማ ተጫዋቾች እረፍታቸውን ከዘመን መለወጫ በአል በኋላ አጠናቀው መስከረም 3 ካምፕ እንዲገቡ ታዘዋል፡፡ ለስራ ጉዳይ ከሃገር ውጭ የሚገኙት የከተማው ከንቲባ ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱም ቃል የተገባላቸው ሽልማት እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡


 

ሶከር ኢትዮጵያ አሰልጣኝ መሰረት ማኒን እና የክለቡን ሃላፊዎች ለማግኘትና ሃሳባቸውን በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ላማካተት ያደረገችው ጥረት ባለመሳካቱ በቀጣይ ፅሁፎች ለማካተት ጥረት ታደርጋለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *