አዳማ ከነማ የዝውውር መስኮቱ ዋና ተዋናይ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው አዳማ ከነማ ከመከላከያ ጋር ውሉ የተጠናቆ የተለያየው ተስፋዬ በቀለን አስፈርሟል፡፡
ጠንካራው ሁለገብ ተከላካይ ከመከላከያ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ የቆየ ሲሆን በቡና እና መከላከያ አብሮት የተጫወተው ሲሳይ ደምሴን ተከትሎ ድሬዳዋ ከነማን ይቀላቀላል ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም ራሱን በአዲስ መልክ እየገነባ ወደሚገኘው አዳማ ከነማ አምርቷል፡፡
ከሴካፋ ውድድር በጊዜ የተሰናበተው አዳማ ከነማ በዘንድሮው ክረምት 9 ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን ‹‹ጃምቦ›› 10ኛው ፈራሚ በመሆን ቡድኑን ተቀላቅሏል፡፡
የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ ከትላንት በስቲያ የጀመረ ሲሆን ቡድኑ ለቀጣዩ አመት አዲስ መልክ ይዞ እንደሚቀርብ አሰልጣኝ አሸናፊ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ቡድኔን በአዲስ መልክ እየገነባሁት ነው፡፡ እስካሁን 10 ተጫዋቾችን የለቀቅን ሲሆን በምትኩም ሌሎች 10 አዳዲስ ተጫዋቾችን አምጥተን የቅድመ ውድድር ዝግጅታችንን ጀምረናል፡፡ የሰበታው ኤርሚያስ ፍስሃን ለማስፈረም ብንፈልግም ቀሪ አንድ አመት ኮንትራት ያለው በመሆኑ የክለቡን ፍቃደኝነት እየጠበቅን ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በድሬዳዋ ተገኝተው የብሄራዊ ሊጉን የማጠቃለያ ውድድር የተመለከቱ ቢሆንም ምንም ተጫዋች እንዳላስፈረሙ ታውቋል፡፡