የተሾመ ታደሰ ጉዳይ ውሳኔ አግኝቷል

ፌዴሬሽኑ ለአንድ አመት ያህል ሲጓተት በነበረው የአርባምንጭ ከተማ እና የአጥቂው ተሾመ ታደሰ ጉዳይ ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

በአርባምንጭ ከተማ ያለፉትን አራት አመታት ቆይታ የነበረው እና በ2009 በአዲስ መልክ ለሁለት አመታት ተጨማሪ ኮንትራንት የፈረመው አጥቂው ተሾመ በዛው የውድድር አመት ግንቦት ወር ላይ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ከራቀ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። ተሾመ በአርባምንጭ ከተማ እስከ ዘንድሮው የውድድር ዘመን ውል ቢኖረውም ክለቡ ከቡድኑ ስብስብ ውጭ አድርጎት በህክምና ላይ የቆየ ሲሆን ያወጣውን ወጪ እና ደሞዙን እንዲከፍለው በተደጋጋሚ ቢጠይቅም በቂ ምላሽን ማግኘት ባለመቻሉ ያለፉትን ሁለት ወራት ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽኑ ወስዶ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት የዲሲፕሊን ኮሚቴው በሁለቱ ወገኖች መሀል ካለው ውል መካከል አንቀፅ 4 እና አንቀፅ 5 ላይ ትኩረት በማድረግ አራት ውሳኔዎችን አሳልፏል። ከውሳኔዋቹ መካከልም ክለቡ የተጨዋቹን ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም እንዲከፍል የተወሰነበት የሚጠቀስ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ባለጉዳዮች ችግራቸውን በግልግል ኮሚቴ በመፍታት ለፌዴሬሽኑ ሪፖርት ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።