ታክቲካዊ ነጥቦች በብሄራዊ ቡድኑ ዙርያ

በሚልኪያስ አበራ እና ዮናታን ሙሉጌታ

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጪው ቅዳሜ ነሃሴ 30 በሲሸልስ መዲና ቪክቶርያ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች መርሃ ግብር አንዱ የሆነውን የሜዳ ውጪ ጨዋታ ያከናውናል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ከወቅቱ የአፍሪካ ሃያል ቡድን አልጄርያ እና በንፅፅር ከሃገራችን እግርኳስ ደረጃ ዝቅ ካሉት ሌሶቶ እና ሲሸልስ ጋር ተመድቦ የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን ሰኔ 7 ቀን በባህርዳር አከናውኖ 2-1 በማሸነፍ 3 ነጥብ መሰብሰቡ የሚታወስ ነው፡፡

የባህርዳሩ የሌሶቶ ጨዋታ እና በናይሮቢ የተደረገው የቻን ማጣርያ የመልስ ጨዋታ የተመለከቱ ቪድዮዎችን የድጋሚ ምልከታ በመውሰድ የቡድኑን ታክቲካዊ ጉዳዮች የሚመለከት ትንታኔ እናቀርባለን፡፡

4-4-2 እና ዋልያዎቹ

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ብሄራዊ ቡድኑን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ 4-4-2ን የብሄራዊ ቡድኑ መደበኛ እና ተመራጭ ፎርሜሽን አድርገውታል፡፡ በእግርኳሱ አለም ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ይህ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ጊዜው ያለፈበት (–ያደረገ) ቢመስልም በዘመናዊው እግርኳስ በትልልቅ የአውሮፓ ቡድኖች ሳይቀር ከቀደሙት ጊዜያት ከነበረው ቅርፅ እና ይዘት መጠነኛ ለውጦችን ይዞ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡

ፎርሜሽኑ በተለያዩ መዋቅሮች (variants) (Flat 4-4-2, Narrow 4-4-2, wide 4-4-2, diamond 4-4-2) ይታወቃሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድ በዚህኛው የሌሶቶ ጨዋታ flat wide 4-4-2ን ተጠቅሟል፡፡ ይህ flat wide 4-4-2 የአጨዋወት ሲስተም 2 ባለ አራት ተጫዋቾችን የያዘ በሜዳው በሜዳው ወርድ ወይም አግድሞሽ የሚደረደሩ ተጫዋቾችን እና ሁለት ተጣማሪ አጥቂዎችን ያሰልፋል፡፡ (two bands of four)

በመከላከል የጨዋታ ሂደት (defending phase) በመስመሮች መካከል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በመድፈን (በተለይ በተከላካይ እና አማካይ መስመሩ መካከል( between the lines) የሚኖረውን ክፍተት በማጥበብ ለተጋጣሚ ቡድን ክፍተት ያለመስጠትን ጥቅም ያስገኛል፡፡ በእርግጥ በፈጣን የሽግግር ሂደት (fast break transition) በተለይ ከማጥቃት ወደ መከላከል ላይ በሚደረገው ሽግግር ሰፊ ተጋላጭ ክፍተትን ይፈጥራል፡፡

እንደ ህፀፅ ከሚወሰዱት የፎርሜሽኑ መገለጫዎች አንዱ እና ዋነኛው ደግሞ በአጥቂዎች በአማካዮች መካከል ያለው ርቀት እና ስፋት ሁለቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች በአብዛኛው በቀጥታ የአግድሞሽ መስመር በመገኘታቸው (lateral parallel positioning) ከአማካይ መስመሩ ርቀው መገኘታቸው ነው ፡፡ ይህ የአጥቂዎቹ የቦታ አያያዝ የተጋጣሚን የመስመር ተከላካዮች ነፃነትን ስለሚሰጥ የባላጋራ ቡድን ፉልባኮች መጠነኛ የሜዳውን ቁመት በነፃነት የመጠቀም እድልን ይሰጣቸዋል፡፡ ሁለቱ የመሃል ሜዳ አማካዮችም (destroyer/passer) ጥምረት ከሆኑ የሚና ውስነት (role specialization) የፈጠራ ክህሎታቸውን ይገድብባቸዋል፡፡ የመስመር አማካዮቹ ደግሞ (traditional wingers) ከሆኑ ወደ መስመሩ ተጠግተው ስለሚጫወቱ በሜዳው ቁመት የሚኖር የተጫዋቾች ጥግግት (lateral compactness) ያሰፋባቸዋል፡፡

የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ እነዚሁ የመስመር አማካዮች (touch line hugging wingers) በመሆናቸው የአጠቃላይ ቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ተገማች (predictable) ይሆናል፡፡

እነዚህና መሰል የፎርሜሽኑ ፅንሰ ሃሳባዊ ችግሮች (conseptual disadvantage) ፎርሜሽኑን ብዙም ተመራጭ ሲያደርጉት አይስተዋልም፡፡ ከዚህ ሌላ በተጋጣሚ ቡድን ፎርሜሽን ላይ የተመሰረተ የመሃል ሜዳ የቁጥር ብልጫ የማስወሰድ ተጋላጭነትን ይፈጥራል፡፡ (በተለይ የተጋጣሚ ቡድን 4-3-3 ፣ 4-5-1 ፣ 3-5-2 እና የመሳሰሉትን በመሃል የሜዳው ክፍል ብዛት ያላቸውን ተጫዋቾች የሚጠቀም ከሆነ)

ብሄራዊ ቡድናችን በሌሶቶው ጨዋታ ይህን ፎርሜሽን ተጠቅሞ ከላይ የጠቀስናቸውን ችግሮች አስተናግዷል፡፡ ቡኑ በምርጡ ብቃቱ ላይ የሚገኘውን ሽመልስን ከሁለቱ የመሃል አማካዮች እንደ አንዱ አድርጎ ማሰለፉ ከተጫዋቹ ሊገኝ የሚችለውን የፈጠራ ክህሎት (creativity) እና አጥቂውን ከአማካዮች ጋር የማገናኘት (linking play) ሚና በተሸለ መልኩ እንዳያገኝ ገድቦታል፡፡ (በተለይም በጨዋታው የመጀመርያ 45 ደቂቃ)

በመጀመርያው አጋማሽ ተጋጣሚያችን የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ እንደመጫወቱ ወደ ኋላ አፈግፍጎ እና የተጋጣሚን ጫና በመቋቋም (siting deep and pressure observation) የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ሲፈጥር ይህንን ለመጠቀም የተዘጋጀ ነበር፡፡ የሽመልስ ወደ ኋላ ያፈገፈገ ሚና የሌሶቶ የአማካይ ክፍል በተረጋጋ መልኩ የመከላከል ቅርፅን እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ ሳላዲን እና ጌታነህም ከአማካይ ክፍላቸው ርቀው እና ተነጥለው ታይተዋል፡፡ በ4-4-2 (4-1-3-2) የተከላካይ አማካይነቱን ሚና የወሰደው ጋቶች አልፎ አልፎ ወደ ፊት እየሄደ ኳስ የያዘን የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ላይ ጫና ለማድረግ ሲጥር ቢታይም ይህ እንቅስቃሴው የተከላካይ ክፍሉን ለተጋጣሚ ጥቃት ተጋላጭ ሲያደርገው ይስተዋል ነበር፡፡

ጋቶች የወደፊቱ የቦታው ሁነኛ ተጫዋች የመሆን አቅም እንዳለው ቢታወቅም የቦታ አጠባበቅ ምልከታው ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየት ይኖርበታል፡፡

1

 

በዚህኛው ጨዋታ ኬንያዎች በኢትዮጵያ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች እና ወደ ኋላ ያፈገፈጉ አማካዮች መካከል የነበረውን ክፍተት በነፃነት ሲጠቀሙበት ተስተውሏል፡፡ በተጋጣሚ ተካላካዮች አቋቋም ወደ ፊት የሚሳቡት አጥቂዎቻችን ከኋለኛው ሰፊ ክፍተት እና ርቀት ስለሚተው ከአማካዮቻቸው ርቀው እና ተነጥለው አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ በተቃራኒው የኢትዮጵያ የተከላካይ መስመር በኬንያ አጥቂዎች ወደ ፊት ተገፍቶ (ተደርጎ) ይታይ ነበር፡፡ ይህ ታክቲካዊ እንቅስቃሴ የተከላካይ አማካዮቹን ጋቶች እና ብሩክን ይበልጥ ወደዷላ ባፈገፈገ ሚና ለ 4ቱ ተከላካዮች ሽፋን እንዲሰጡ ሲያስገድዳቸው ይታያል፡፡ በዚህኛው ጨዋታ ብሄራዊ ቡድናችን ውጤትን አስጠብቆ ለመውጣት በመከላከል ስራ ላይ ባተኮረው ታክቲካዊ አቀራረቡ መጠነኛ ሙገሳ ሊቸረው ቢገባም በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረገው ሽግግር ላይ (defence-attack transition) ግን ጉልህ የሚባል ችግር ታይቶበታል፡፡ እንደ ማሳያ እንዲሆን በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ በ42ኛው ደቂቃ ላይ በእኛ የሜዳ ክልል ለኬንያ የተሰጠችን የቅጣት ምት በመከላከል ግድግዳው መስመር ከተመለሰ በኋላ በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሽግግር የኬንያ የግብ ክልል የደረሰችን ኳስ በኃይሉ ለመሳት በሚከብድ መልኩ አምክኗታል፡፡ ኳሷን ከማምከኑ በፊት ግን የቡድን አጋሮቹ የማጥቃት ማእዘናትን ሲፈጥሩለትና የመቀባበያ አማራጮችን ሲያበዙለት አልተስተዋለም፡፡

2

 

የቅብብሎቻችን መዳረሻ እና ስኬታማነታቸው

በኢትዮጵያ እግርኳስ የቅብብሎቻችን ስኬታማነት እና መዳረሻ ቦታቸውን ማስገንዘብ የሚያስችል የቴክኖሎጂ እገዛ ባይኖርም የተጫዋቾቻችንን ቅብብሎችን በትክክል የመፈፀም ችግር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የዚህ ችግር አይነተኛ መገለጫዎቹ የቅብብሎቹን ፍጥነት እና ርቀት አመርቂ አለመሆን ብቻ ሳይሆ ቅብብሎቹ የሚፈፀሙበት ቦታ ወይም መዳረሻም ሌላኛው ማሳያ ይሆናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የቅብብሎቻችን ትክክለኛነት (passing accuracy) ችግር ከአቀባዮቹ እይታ (vision) እና ከተቀባዮቹ የቦታ አያያዝ (positioning) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ይህ በክለቦቻችን የተለመደው የተጫዋቾቻችን ችግር በብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችም ላይ አሉታዊ ተፅእኖው እየጎላ ይገኛል፡፡ ተጫዋቾቻችን በተጨናነቀ ቦታ ላይ ሆነው ጓደኞቻቸው ቅብብሎችን እንዲፈፅሙላቸው ይጠብቃሉ፡፡ አቀባዮቹ ደግሞ የተቀባዩን ቦታ ሳያስተውሉ እና ልኬታቸውን ሳይገምቱ ቅብብሎችን ይተገብራሉ፡፡ ብዙ ኳሶቻችን በተጋጣሚ ተጫዋቾች የሚቋረጡበት (intercept የሚደረጉበት) ምክንያትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በሌሶቶው ጨዋታ 16ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ለሳላዲን በግራ መስመር ኳስን ሲያቀብለው ሳላዲን ነፃ አልነበረም፡፡ በዚሁ ጨዋታ ላይ በ18ኛው ደቂቃ ጌታነህ በላይኛው የሜዳ ክፍል በቀኝ መስመር ኳስን የሚያቀበለው ሲያጣም ተስተውሏል፡፡ ከመስመሩ በአግድሞሽ ለሚላኩ ረጃጅም ኳሶች (long diagonal passes) ትክክለኛነት የአቀባዩም የርቀት ግምት (distance assumption) እና የተቀባዩ የቦታ አጠባበቅ (positional display) ወሳኝ ነው፡፡

ንዝህላልነት የሚታይባቸው ቅብብሎቻችን ስኬትን ካለማምጣት በዘለለ ጉዳታቸው የሚያመዝንባቸው አጋጣሚዎች አይቀሬ ናቸው፡፡ ስለ ቅብብሎቻችን ስኬት ትክክለኛነት እና ልኬት የምንጨነቅበት ጊዜ ሊኖረን ይገባል፡፡

 

3

 

4-2-3-1 ብንተገብርስ

በቀድሞው ስፔናዊ የአልሜርያ አሰልጣኝ ሆዋን ማኑኤል ሊዮ በ1990ዎቹ የመጀመርያ አመታት ወደ እግርኳ አለም እንደመጣ የሚነገርለት ይህ ፈርሜሽን ያለፉት 15 አመታት የዘመናዊ እግርኳስ መገለጫዎች እንደ አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በአንፃራዊ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ‹‹ስኬት›› የሚመሰገነው የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድንም በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ይህን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን ተጠቅሟል፡፡

ፎርሜሽኑ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የሚዛናዊነት ጠቀሜታ እንዳለው ይገለፃል፡፡ በመከላከልም ሆነ በማጥቃት የአጨዋወት ሂደት ላይ የቡድን የሜዳ ላይ ሚዛንን ለመጠበቅ የሚያስችል ስርአትን ስለሚያስገኝ አሰልጣኞች አብዛኛውን ጊዜ ቦታ ይሰጡታል፡፡ በሜዳው የላይኛው ክፍል የበዙ የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾችን ስለሚያስገኝና ብቸኛ የፊት መስመር ተሰላፊ አጥቂን በብዙ አቅጣጫዎች ማገዝ የሚያስችል መዋቅር ስላለው የማጥቃት አጨዋወት ላይ ሁነኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

ከብቸኛ አጥቂው ጀርባ በመሃል ሜዳው ቁመት የፈጠራ ክህሎት የታደለን እና የተጋጣሚን ተከላካይ ክፍል አደረጃጀት በፈጠራ ክህሎቱ ማስከፈት የሚችልን የ10 ቁጥር ሚና የሚጫወት የጨዋታ አቀጣጥ ማስገኘቱ ደግሞ ሌላኛው የማጥቃት አጨዋወት ጠቀሜታ ነው፡፡

በማጥቃት አጨዋወት ላይ ይበልጥ በማተኮር የሚያዘወትሩት የመስመር አማካዮችም የተጋጣሚን የመስመር ተከላካዮች የፊት ለፊት የማጥቃት እንቅስቃሴ (overlapping movement) ባለበት ቦታ የማስቀረት (stifle የማድረግ) አቅም የሚፈጥርላቸውን flank position መያዝ ያስችላቸዋል፡፡ በተለምዶ በ4-2-3-1 ፎርሜሽን የሚገኙት የተከላካይ አማካዮችም double pivot ሚናን መተግበር የሚያስችላቸው ቦታ እና የማሰቢያ ጊዜን የሚያገኙበት ሆኔታ አላቸው፡፡ በአብዛኛው በ single pivot የሚጫወቱ የተከላካይ አማካዮች በሜዳው ወርድ ወይም ስፋት የሚያደርጉት የጎንዮሽ እንቅስቃሴ አድካሚ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህም ብዙውን ጊዜ back four ለተጋጣሚ ቡድን ተጋላጭ እንሆ ያደርገዋል፡፡ double pivot ደግሞ ከተከላካይ ክፍሉ ፊት በመገኘት ሰፊውን የጎንዮሽ ርቀት የመሸፈን ግዴታን ለሁለት የተከላይ አማካይ ሚና ተጫዋቾች በማካፈል የተራጀ የመከላከል አቅምን ለአጠቃላይ ቡድኑ የማስገኘት አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም በጥሩ ብቃቱ ላይ የሚገኘውን የሽመልስ በቀለን የፈጠራ ክህሎት ለመጠቀምና ከሌሎች የመስመር አማካዮች ምርጡን ለማግኘት ይህንን ፎርሜሽን በቅዳሜው ጨዋታ ቢተግብሩ ተጠቃሚነቱ የተሻለ ሊሆን ይችላል ሳላዲን በርጊቾን በዲሲፕሊን ቅጣት ያጣውንና የመሃል ተከላካይ ጥምረቱ ላይ አዲስ ተጫዋች የሚያሰልፍ መሆኑ (ምናልባትም ዋሊድ አታ) ከጨዋታ ጨዋታ መጠነኛ የመደራጀት አቅምን ፈጥሮ የነበረው የተከላካይ ክፍል ስለሚለወጥና ለመግባባትና የተጠናከረ የመከላከል መስመር ይኖረናል ብሎ በድፍረት መናገር ባለመቻሉ ሲሸልስን የሚገጥመው የመከላከል ክፍላችን ከፍተኛ ሽፋን የሚሰጠው የአማካይ ክፍል ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ከለላ ለማስገኘት ደግሞ 4-2-3-1ን መጠቀም አዋጭ መንገድ ነው፡፡

4-2-3-1 ፎርሜሽን ባለ 4 መስመር (four band) የተጫዋቾች አደራደር ቅርፅ ያለው በመሆኑ ከፍ ያለ የሜዳ ክፍል ለመሸፈን ከመቻሉ በላይ በተጫዋቾች መስመሮች (በሜዳው ወርድ) መካከል የሚኖረውን ርቀት በማጥበብ ተጫዋቾች ተቀራርበው የሚጫወቱበትን እድል ይሰጣል፡፡ ይሕም በተጋጣሚ ሜዳ የሚኖርን ድካም ለመቀነስና ውጤትን አስጠብቆ ለመውጣት ይረዳናል፡፡

መልካም እድል ለብሄራዊ ቡድናችን

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *