ኢትዮጵያ ከሲሸልስ ነጥብ ተጋራች

ሲሸልሽ እና ኢትዮጵያ በቪክቶርያ ዩኒቲ ስታድየም ባደረጉት የምድብ 10 ሁለተኛ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰላለፍ ይህንን ይመስል ነበር፡-

ታሪክ ጌትነት

ስዩም ተስፋዬ (በ54ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሯል) ፣ ዋሊድ አታ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ተካልኝ ደጀኔ

ኤፍሬም አሻሞ ፣ ጋቶች ፓኖም (ሙሉአለም መስፍን) ፣ ሺመልስ በቀለ ፣ ኡመድ ኡኩሪ (አስቻለው ግርማ)

ጌታነህ ከበደ (ባዬ ገዛኸኝ) እና ሳላዲን ሰኢድ(አምበል)

 

የእለቱ ዳኞች ዘግይተው በመድረሳቸው ጨዋታው ይጀመራል ከተባለበት 9፡30 በ30 ደቂዎች ዘግይቶ 10፡00 ላይ ተጀምሯል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይም ሬኒክ ሌኒ ፣ ኔልሰን ሎውረንስ እና አቺሌ ሂኔርቲ አደገኛ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡

በ23ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ የግብ ክልል ተካልኝ ደጀኔ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ይፍፁም ቅጣት ምት በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኔልሰን ሎውረንስ ወደ ግብነት ቀይሮ የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን 1-0 እንዲመራ አስችሎታል፡፡

የኔልሰን ሎውረንስ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ - ፎቶ በሊባኖስ ዮሃንስ
የኔልሰን ሎውረንስ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ – ፎቶ በሊባኖስ ዮሃንስ

ከግቡ መቆጠር በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ያለመረጋጋት እና የውህደት ችግር ታይቶበታል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በሲሸልስ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስም ችለዋል፡፡ በ2ኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች የሲሸልሱ ትሬቨር ዊዶት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

በ54ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ ኢትዮጵያን አቻ የምታደርግ ግብ በማስቆጠር ዋልያዎቹን ወደ ጨዋታው መልሷቸዋል፡፡ ከግቧ በኋላ ሲሸልሶች ወደ ግብ ክልላቸው ተጠግተው መከላከልን ሲመርጡ ኢትዮጵያ በማጥቃት ወደ ግብ በመቅረብ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርጋለች፡፡ በተለይም በ78ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰኢድ እጅግ ለግብ የቀረበች ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው የግብ ማግባት እድል የሚቀስ ነበር፡፡

ሲሸልሶች በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ሰአት በማባከን ጨዋታውን በአቻ ውጤት ለመጨረስ የጣሩ ሲሆን ተሳክቶላቸው ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጊዜያዊነት ምድቡን መምራት ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ ከ2 ጨዋታ 4 ነጥብ ይዛ አንደኛ ደረጃን ስትይዝ ነገ ከሌሶቶ ጋር 2ኛ የምድብ ጨዋታዋን የምታደርገው አልጄርያ በ3 ነጥብ ትከተላለች፡፡ ሲሸልስ በ1 እንዲሁም ሌሶቶ በ0 ነጥብ የዘው ይከተላሉ፡፡

የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ከ5 ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ ተጋርታለች፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3ኛ የምድብ ጨዋታውን ከአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በሜዳው ያደርጋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *