የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሳምንቱ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በዚህ ሳምንት በምድብ ሀ የ22ኛ ሳምንት፣ በምድብ ለ ደግሞ የ21ኛ እና የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ከቅዳሜ እስከ ሰኞ የነበሩ ጨዋታዎችን በዚህ መልኩ ተመልክተናቸዋል። 

ቅዳሜ

በዚህ እለት ምድብ ሀ ላይ 3 ጨዋታዎች ተደርገዋል። ወሎ ኮምቦልቻ ከኢትዮጵያ መድን ያደረገውን ጨዋታ 2-0 በማሸነፍ እያሳየ ባለው መሻሻል ቀጥሏል። ሙክታር ከድር እና ሄኖክ ጥላሁን ደግሞ የጎሎቹ ባለቤቶች ናቸው። ሌላው በሁለተኛው ዙር የተሻሻለው ነቀምት ከተማ ደካማ አቋም እያሳየ የሚገኘው ሱሉልታ ከተማን አስተናግዶ በገዛኸኝ ባልጉዳ ጎሎች 2-0 በመርታት ከወራጅ ቀጠናው መራቅ ችሏል። አክሱም ላይ አክሱም ከተማ ከ ኢኮስኮ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በምድብ ለ የ21ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ቅዳሜ አንድ ጨዋታ ሲከናወን ዲላ ከተማ ከሀደለያ ሆሳዕና ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
እሁድ
(በሚካኤል ለገሰ)

በምድብ ሀ መሪው ባህርዳር ነጥብ ሲጥል የምድብ ለ ጨዋታዎች ጎል አልባ እለት አሳልፈዋል።

ባህርዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል። አሰልቺ እና ብዙ የጎል ሙከራዎች ያልተስተዋሉበት ሆኖ ያለፈው ጨዋታ የኳስ  ቅብብሎች ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡበት የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ያልታየበት ሆኗል። በ22ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ፌዴራል ፖሊሶች በጌትነት ታፈሰ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። ግቧ ስትቆጠር የጣና ሞገዶቹ ግብ ጠባቂ ስህተት ጎልቶ የታየ ሲሆን በጊዜው  ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ከግብ ክልሉ በመውጣቱ እና ኳሷን ለማዳን ጥረት ባለማድረጉ ምክንያት ጎሏ ተቆጥራለች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ተጋባዦቹ በፍቃዱ እና በወሰኑ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ጫናዎችን ተጋጣሚያቸው ላይ ያደረጉ ሲሆን በ31ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አግኝቶ አቻ መሆን ችለዋል። ፍቃዱ ወርቁ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ወሰኑ ዓሊ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑ ከመመራት ቶሎ እንዲያገግም ማድረግ ችሏል።

ከእረፍት መልስ ባህርዳር ከተማዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን በተቃራኒው ፌዴራል ፖሊሶች ተከላክለው በሁለቱ የፊት መስመር አጥቂዎቻቸው ፍጥነት በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጥሚዎች የሚገኙ የግብ ማግባት እድሎችን ለመጠቀም ሲጥሩ ተስተውሏል። በ70ኛው ደቂቃ ወሰኑ ዓሊ ከመስመር ለሙሉቀን ታሪኩ ያሻገረለትን ኳስ ሙሉቀን በግንባሩ ሞክሮ ለጥቂት ኳሷ ወደ ውጪ የወጣችበት ባህርዳሮችን መሪ ልታደርግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች። ከአራት ደቂቃ በኃላ ባለሜዳዎቹ ፌደራል ፖሊሶች በግብ አስቆጣሪያቸው ጌትነት ታፈሰ የቅጣት ምት ኳስ ብቸኛ የሁለተኛ አጋማሽ የግብ ማግባት አጋጥሚያቸው ሲሆን ምንተስኖት አሎ ኳሷን ወደ ውጪ አውጥቷታል። የጨዋታው መገባደጃ አካባቢ አካላዊ ጉሽሚያዎች የተስተዋለ ሲሆን ተጨማሪ ጎሎች ሳይቆጠሩ አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በእለቱ በዚህ ምድብ ለተደረገ መርሐ ግብር ቡራዩ ከተማ ከአውስኮድ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ሲለያዩ ደሴ ላይ ሊደረግ የነበረው የደሴ ከተማ እና የየካ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።

በምድብ ለ ብቸኛ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታ በካፋ ቡና እና ናሽናል ሴሜንት መካከል ተካሂዶ ካፋ ቡና 1-0 በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ መጠጋት ችሏል። በዚሁ እለት በተካሄዱ የ21ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ደግሞ መሪው ደቡብ ፖሊስ ወደ ጅማ አቅንቶ ከጅማ አባ ቡና ያለ ጎል አቻ በመለያየት መሪነቱን የማጠናከር እድል ሲያመክን ሰበታ ላይ ሀምበሪቾን የገጠመው ወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ ያለ ጎል ጨዋታውን አጠናቋል።


ሰኞ

(በአምሀ ተስፋዬ)

በምድብ ሀ በሊጉ የመጀመርያ ደረጃዎች የሚገኙ ቡድኖችን እርስ በእርስ ያገናኙ ጨዋታዎች ተከናውነው አአ ከተማ ወደ ድል ሲመለስ ለገጣፎ እና ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል። የፌዴሬሽኑ ክፍተትም ታይቶበታል።
ከቅዳሜ ወደ ሰኞ የተሸጋገረው የአአ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ 4:00 ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም የፀጥታ ኃይል በቦታው ባለመገኘቱ ጨዋታው ለአንድ ሰዓት ያህል ዘግይቶ ለመጀመር ተገዷል። ብርቱ የመሸናነፍ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በመጀመሪያው 20 ደቂቃዎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት አዲስ አበባዎች በፍቃዱ ዓለሙ እና ላኪ ሳኒ የግብ ሙከራ አድርገዋል። በ22ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታዎች በዳንኤል ታደሰ አማካኝነት ያደረጉት ሙከራም ተጠቃሽ ነበር። በ26ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ምንያምር ያሻማውን ኳስ ፍቃዱ አመቻችቶ ሲያሳልፍለት ሙሀጅር መኪ በአግባቡ በመጠቀም ወደ ግብነት ለውጦታል። ከግቡ ባኋላ ተጭነው ለመጫወት የሙከሩት ሰበታዎች በሄኖክ መሀሪ ፤ ዳንኤል እና ክንዳለም ፍቃዱ ያደረጉት ሙከራ በመጅመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ ነበር።

ከዕረፍት መልስ በሰበታ በኩል በ72ኛው ደቂቃ ላይ እና በ80ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ታደሰ ወደግብ መለወጥ የሚችልባቸውን እድሎች ሳይጠቀም ሲቀር በአዲስ አበባ በኩል ሙሀጅር መኪ እና ገናናው ረጋሳ ያመከኗቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ናቸው። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በአአ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በቀጣይ ሊደረግ የታሰበው የሽረ እና ለገጣፎ ጨዋታ በድጋሚ በፀጥታ ኃይል ባለመገኘታቸው ለ46 ደቂቃ ዘግይቶ ተጀምሮ 1-1 በሆነ ቻ ውጤት ተጠናቋል። በ29ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል አስማማው በፍፁም ቅጣት ምት ለገጣፎን ቀዳሚ አድርጎ ቡድኑን እስከ ጨዋታው መገባደጃ መሪ ማድረግ ቢችልም ልደቱ ለማ በተጨማሪ ደቂቃ የቀድሞ ክለቡ ላይ ያስቆጠረው ጎል ሽረ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል።

በምድብ ለ ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ነገሌ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 10:00 ላይ ተካሂዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የደረጃ ሰንጠረዥ

ምድብ ሀ

ምድብ ለ