የ17 እና 20 ዓመት በታች ማጠቃለያ ውድድሮች የሚካሄዱበት ቦታ ታውቋል

2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች እና 20 ዓመት በታች ሊጎች የማጠቃለያ ውድድሮች በባቱ ከተማ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ከሐምሌ 5 እስከ 15 ጨዋታዎቹ የሚካሄዱበት ቀናት ናቸው።

ሁለቱም ውድድሮች በሁለት ምድቦች ተከፍለው እየተካሄዱ የሚገኙ ሲሆን የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ባለፈው ሳምንት ተጠናቋል። ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ደግሞ በቀጣይ ሳምንት በሚደረጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ፍፃሜውን የሚያገኝ ይሆናል።

በባቱ በሚደረገው የማጠቃለያ ውድድር ከየምድቡ 5 ቡድኖች ይካፈላሉ የተባለ ሲሆን በ20 ዓመት በታች ውድድር ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ መድን፣ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ እና ድሬዳዋ ከተማ ከምድብ ሀ ፤ ሀዋሳ ከተማ፣ ደደቢት፣ ወላይታ ድቻ፣ አአ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምድብ ለ ወደ ማጠቃለያ ውድድሩ ያለፉ ናቸው።

አንድ ሳምንት በሚቀረው ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከምድብ ሀ ማራቶን፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ፤ ከምድብ ለ ደግሞ አፍሮ ጽዮን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አካዳሚ እና ወላይታ ድቻ ወደ ማጠቃለያው ውድድር ያለፉ ቡድኖች ናቸው።