መቐለ ከተማ ጋብርኤል አህመድን አስፈረመ

መቐለ ከተማ ጋናዊው አማካይ ጋብርኤል አህመድ “ሻይቡ”ን ማስፈረሙን አስታውቋል።

ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት 4ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው መቐለ ከተማ በዚህ ሳምንት ሁለት አማካዮቹን (ሐብታሙ ተከስተነ ወደ ፋሲል፣ ጋቶች ፓኖምን ወደ ኤል ጎውና) የሸኘ ሲሆን የቦታውን ክፍተት ለመሸፈን ገበያ ወጥቷል። በዚህም ጋናዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ጋብርኤል አህመድን ማስፈረሙን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ጋብርኤል በ2004 የውድድር ዓመት ደደቢትን በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ወዲህ የሊግ ዋንጫ ባነሳበት የሰማያዊዎቹ ቤት እስከ 2007 ቆይቶ ወደ ንግድ ባንክ ያመራ ሲሆን ከባንክ የሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ለሀዋሳ ከተማ ተጫውቷል።

ክለቡ በመጪዎቹ ቀናት ከአሰልጣኝ ቅጥር በተጨማሪ ከክለቡ ጋር የሚቀጥሉ ተጫዋቾች ውል ማራዘም እንደሚጀምርና አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንደሚንቀሳቀስ ይጠበቃል።