የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌድሬሽን የሚያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (city cup) ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡
ይህ ውድድር መስከረም 22 እንደሚጀምር የአዲ አበባ እግርኳስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዮናስ ሀጎስ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ 8 ክለቦችን የሚያሳትፈው ይህ ውድድር ለ2 ሳምንታት ያክል (ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 7) በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚከናወንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ውድድሩ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት የሚደረግ በመሆኑ ክለቦች ከቅድመ ውድድር ዝግጅት በኋላ አቋማቸው ምን እንደሚመስል የሚለኩበት እንዲሁም አዳዲስ ተጫዋቾች በቡድናቸው የሚኖራቸው ሚና ምን እንደሆነ የሚያውቁበት ውድድር በመሆኑ ጠቃሚነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከአቋም መለኪያነቱ በተጨማሪም ክለቦችን በገንዘብ ረገድ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ይህን ውድድር ለማድረግ ስድስቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ መከላከያ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ኤሌክትሪክ ፍቃደኛ የሆኑ ሲሆን ሁለቱ ተጋባዥ የክልል ክለቦችን ጨምሮ የስፖንሰር እና ሌሎች ጉዳዮችን በዚህ ሳምንት ፌዴሬሽኑ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደሚያስታውቅ ታውቋል፡፡
ፌዴሬሽኑ ለክለቦቹ እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን ከሚገኘው ገቢ (ከስታድየም ትኬት ሽያጭ እና ከስፖንሰር) ላይ በመቶኛ ይካፈላሉ፡፡
ተሳታፊ የሚሆኑት ክለቦች የሚከፋፈሉት ገንዘብ በመቶኛ ይህንን ይመስላል
-1ኛ የሚወጣው ክለብ 15%
-2ኛ የሚወጣው ክለብ 10%
-3ኛ የሚወጣው ክለብ 7%
-4ኛ የሚወጣው ክለብ 4%
-5ኛ የሚወጣው ክለብ 3%
-6ኛ የሚወጣው ክለብ 3%
በተጋባዥነት ውድድሩ ላይ የሚካፈሉት ሁለቱ የክልል ክለቦች ግን እንደ ባለፈው አመት ሁሉ የገንዘብ ክፍፍል ውስጥ እንደማይካተቱ አቶ ዮናስ ሀጎስ ተናግረዋል፡፡
ያለፈው አመት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በካስትል ቢራ ስፖንሰርነት የተደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ ቡናን በመለያ ምቶች አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡