ወልዋሎ የሦስት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

በዝውውር መስኮቱ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ወልዋሎ የፕሪንስ፣ ሳምሶን ተካ እና ኤፍሬም ኃይላትን ውል ማደሱ ታውቋል። 

ቡርኪና ፋሷዊው የመስመር አጥቂ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ወደ ወልዋሎ ካመራ በኋላ መልካም ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን ክለቡ በሊጉ እንዲቆይ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ተጫዋቹ የውል ጊዜው ሰኔ 30 መጠናቀቁን ተከትሎ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ አገልግሎት ሳይሰጥ መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ውሉን ለአንድ ተጨማሪ ዓመት አድሷል።

ወልዋሎ ውላቸውን ያደሰላቸው ሌሎች ተጫዋቾች ሳምሶን ተካ እና ኤፍሬም ኃይላት ናቸው። አመዛኙን የውድድር ዘመኑን በተጠባባቂ ወንበር ተቀምጠው ያሳለፉት ሁለቱ ተጫዋቾች ለተጨማሪ አንድ ዓመት ውላቸውን አድሰዋል።

ወልዋሎ በክረምቱ ካስፈረማቸው አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን ጨምሮ የ7 ተጫዋቾችን ውል አድሷል።