ሴቶች ዝውውር | መከላከያ አራት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊው መከላከያ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በተከላካይ መስመር ላይ ያተኮረ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅ አምስት ተጫዋቾች ደግሞ ውላቸውን ማደሳቸውን ክለቡ ገልጿል።

ወደ መከላከያ ካቀኑት ተጫዋቾች መካከል መሠሉ አበራ አንዷ ናት። መሠሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት የብሔራዊ ቡድን ቦታ ማግኘት የቻለች ሲሆን በሴካፋ እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች ላይ ተሰልፋ ከረጅም ርቀት ግሩም ጎሎችን በማስቆጠር የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችላለች።

ገነት አክሊሉ ሌላዋ ፈራሚ ስትሆን የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በደደቢት ያሳለፈች ግብ ጠባቂ ናት። በሲዳማ ቡና መልካም የውድድር ዘመን ያሳለፈችው አማካይዋ ጸኃይነሽ ዱላ እና የአአ ከተማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረችው ምህረት ኃይሉ ሌሎች የጦሩ አዳደስ ፈራሚዎች ናቸው።

በቀድሞው የወንዶች ቡድኑ አሰልጣኝ ምንያምር ጸጋዬ የሚመሩት መከላከያዎች የአምስት ነባር ተጫዋቾችን ውል አድሰዋል። ግብ ጠባቂዋ ሳራ ብርሀኑ፣ ተከላካዮቹ ገነት ሰጠ እና አትክልት አሸናፊ እንዲሁም አጥቂዎቹ ኄለን ሰይፉ እና ኄለን እሸቱ ውላቸውን ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ማደሳቸው ታውቋል። ሀና ቱልጋ (ተከላካይ) ፣ አክበረት ገብረፃዲቅ (አማካይ) እና ኄለን (ግብ ጠባቂ) ደግሞ ከክለቡ የለቀቁ ተጫዋቾች ናቸው።