አስናቀ ሞገስ ዳግመኛ ወደ ባህር ዳር ከተማ አምርቷል

በ2009 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 65 ነጥቦችን በመሰብሰብ ገና በጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው ባህር ዳር ከተማ የሊጉ ተሳታፊ መሆኑን ካወቀ በኃላ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ እየቀላቀለ ይገኛል።

በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሚመራው ቡድኑ ከዚህ ቀደም አምስት ተጨዋቾችን በይፋ ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ስድስተኛ ተጨዋቹን ማግኘቱ ተገልጿል። ተጨዋቹ በ2008 ከኢትዮጵያ ቡና በውሰት ወደ ባህር ዳር ከተማ አቅንቶ አንድ ዓመት ያገለገለው እና ከአንድ አመት ቆይታ በኃላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ቡና በመመለስ ሁለት አመታትን ከቡናማዎቹ ጋር ያሳለፈው አስናቀ ሞገስ ነው። ተጨዋቹ በቀጣይ ለአንድ ዓመት ለባህር ዳር ለመጫወት መፈረሙ ተረጋግጣጧል።

በመስመር አጨዋወታቸው የሚታወቁት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከአስናቀ በፊት ሁለት የመስመር አጥቂዎች እና አንድ የመስመር ተከላካይ ማስፈረማቸው እንደ ዘንድሮ ሁሉ በቀጣይ ዓመትም ይህንን የመስመር አጨዋወት ዘይቤ ለማጠናከር እንዳሰቡ የሚያመላክት ሆኗል።

ቡድኑ ከዚህ በፊት ካስፈረማቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ ደረጄ መንግስቱ፣ ፍቃዱ ወርቁ፣ ግርማ ዲሳሳ፣ ተስፋሁን ሸጋው፣ ወንድሜነህ ደረጄ፣ ደረጄ መንግስቱ እንዲሁም አቤል ወዱ እስካሁን ውል ያደሱ ተጨዋቾች ናቸው።