የተጠናቀቀው የውድድር ዘመንን በሁለት ሆላንዳውያን አሰልጣኞች (ማርት ኑይ እና ሬኔ ፌለር)ያጠናቀቀው የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉትን ሁለት ወራት ካለ ዋና አሰልጣኝ ቆይቶ የብራዚላዊውን አሰልጣኝ ቅጥር ይፋ አድርጓል፡፡
በተለያዩ ሃገሮች ተዟዙሮ የመስራት ልምድ ያላቸው ዶስ ሳንቶስ በወጣት ቡድን ደረጃ በብራዚሎቹ ታላላቅ ክለቦች ቦታ ፉጎ እና ቫስኮ ዳጋማ ሰርተዋል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ የጉያና የካይማን ደሴት እና የባህማስ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠኑ ሲሆን የጃማይካዎቹን ቪሌጅ ዩናይትድ እና ሞንቴጎ ቤይ ዩናይትድ እንዲሁም የታንዛንያው ሲንባን አሰልጥነዋል፡፡
የ49 አመቱ አሰልጣኝ ዶ ሳንቶስ ለቀጣዮቹ 2 አመታት ፈረሰኞቹን ለማሰልጠን የተስማሙ ሲሆን ዛሬ ወደ አዳማ በመጓዝ የአሰልጣኝነት ስራቸውን ይጀምራሉ ተብሏል፡፡
አሰልጣኙ ከስምምነቱ በኋላ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ድረ-ገፅ በሰጡት አስተያየት “ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማሰልጠን በመብቃቴ እጅግ ኩራት ይሰማኛል፡፡የሲምባ አሰልጣኝ በነበርኩበት ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስን ታንዛኒያ ላይ በተካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ላይ የማየት እድሉ ነበረኝ፡፡ በጊዜው ጥሩ እግር ኳስን ሲጫወቱ ተመልክቼያለሁ፡፡የዚህ ታላቅ ክለብ አባል በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል ” ብለዋል፡፡
“የሁላችንም አላማ አንድ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው የምንለፋው፡፡እኔም ልክ እንደ ደጋፊው እና እንደ ቦርድ አባላቱ ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተሰብ በመሆን ቡድናችንን ሁላችንም ወደምንፈልገው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ለመምራት እንጥራለን፡፡ይህንን ለማሳካት ሁላችንም በአንድነት መቆምና ጠንካራ ስራን መስራት አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዛሬዋ እለት አንስተን መንቀሳቀስ ይኖርብናል” ሲሉ ስለ ቀጣይ አላማቸው አስረድተዋል፡፡
ፎቶ – St George