የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ለኢትዮጵያ ጨዋታ 23 ተጫዋቾችን ለይቷል

በአሠልጣኝ ጆን ኪስተር የሚመራው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ጳጉሜ 4 በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ የተመረጡ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን አሳውቋል። በሃገሪቱ እግርኳስ ማህበር ውስጥ በተፈጠረው ችግር እና በኢቦላ ወረርሺኝ ምክንያት በሴራሊዮን ላለፉት 4 ዓመታት የውስጥ ሊግ ውድድር መደረግ አለመቻሉ በስራቸው ላይ እክል እንደፈጠረባቸው ሲገልፁ የቆዩት አሠልጣኝ ኪስተር ይህንን በሚያንፀባርቅ መልኩ በሃገር ውስጥ የሚጫወቱ 2 ተጫዋቾችን ብቻ በቡድኑ አካትተዋል።

በእንግሊዝ የሚጫወቱትን አማዱ ባካዮኮ (ኮቨንትሪ ሲቲ)፣ ኦስማን ካካይ (ክዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ) እና አልሃጂ ሲሴይ (ብሪስቶል ሲቲ) ጨምሮ 7 የሚደርሱ ተጫዋቾች ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ የደረሳቸው ሲሆን በስዊዘርላንድ ኤፍሲ ዙሪክ የሚጫወተው አምበሉ ኡማሩ ባንጉራ ከጉዳት አገግሞ መመለስ መቻሉ ለአሠልጣኙ መልካም ዜና ሆኗል። ለጊዜው ክለብ ባይኖረውም ሴራሊዮን ኬንያን 2-1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ጥሩ በመንቀሳቀስ ግብ ማስቆጠር የቻለው የ34 ዓመቱ አማካይ ጁሊየስ ዎባይ በቡድኑ ውስጥ ተካቷል።

በቡድን ምርጫው ዙሪያ ለቢቢሲ ስፖርት አስተያየታቸውን የሰጡት አሠልጣኝ ጆን ኪስተር “መጀመሪያ 35 አባላት ያሉት ቡድን ነበር የመረጥነው። ይህ ቡድን ለኢትዮጵያ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ከፊታችን ላሉት 4 ጨዋታዎች ታስቦ ነው የተመረጠው። አሁን የመጨረሻው ቡድን ውስጥ መግባት ያልቻሉ ተጫዋቾች በቀጣይ ላሉት ጨዋታዎች የቡድኑ አባል የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው፤” ሲሉ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና ለካዛኪስታኑ ካይሳር ኤፍ ሲ የሚጫወተው የተከላካይ አማካይ ጆን ካማራ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ እንደተዘጋጀ እና ተጫዋቾቹም ለዓመታት ያካበቱት ልምድ ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ እንደሚረዳቸው ተናግሯል። የሊዮን ኮከቦች በሚል ስም የሚታወቀው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን በሀዋሳ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በማሸነፍ ከጋና ጋር ከሚያደርገው ከባድ የደርሶ መልስ ፍልሚያ በፊት ነጥቦችን መሰብሰብ እንዳለበት ነው ካማራ የገለፀው።

“ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኬንያ እና ጋና ጋር በቀጣይ የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ከባድ ቢሆኑም በችሎታችን ማመን አለብን። በመጀመሪያ ከጠንካራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ስንጫወት በጥሩ መንፈስ እና አስተሳሰብ መሆን ይኖርበታል። ቡድናችን በሁሉም ስፍራ ጥራት ስላለው ጥሩ ውጤት ማምጣት እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ። ጨዋታውን ለማሸነፍ ጠንክረን መስራት እና ከጋና ጋር ካሉን ጨዋታዎች በፊትም ዕድላችንን ማስፋት ይኖርብናል፤” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የ2019 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ 6 ሁለተኛ ጨዋታዎች ጳጉሜ 4 ቀን ሲደረጉ ኢትዮጵያ ሴራሊዮንን፣ ኬንያ ደግሞ ጋናን ያስተናግዳሉ። ምድቡን ጋና በ3 ነጥብ እና 5 የግብ ክፍያ ስትመራ በአፍሪካ ዋንጫው ከተሳተፈች 23 ዓመታትን ያስቆጠረችው ሴራሊዮን በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ኬንያ ያለምንም ነጥብ እና አንድ የግብ ዕዳ ሶስተኛ፤ ከ2013 በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ እየተጫወቱ የሚገኙት ዋሊያዎቹ ደግሞ ያለ ነጥብ በ5 የግብ ዕዳ የምድቡ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።

ለሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ተጫዋቾች

ግብ ጠባቂዎች: ሰለሞን ዞምቦ ሞሪስ (ሮዴዎ – ፈረንሳይ)፣ አልሃጂ ሲሴይ (ብሪስቶል ሲቲ – እንግሊዝ)፣ መሐመድ ካማራ (ጆሃንሰን – ሴራሊዮን)

ተከላካዮች: ኡማሩ ባንጉራ (ኤፍሲ ዙሪክ – ስዊዘርላንድ)፣ ዴቪድ ሲምቦ(ኪረሚቴን ስፖር – ቱርክ) ፣ ሃሰን ሚላ ሲሴይ (ላትሂ – ፊንላንድ)፣ አቡ ሱማ (ክለብ የለውም)፣ ኦስማን ካካይ (ኪውፒአር – እንግሊዝ)፣ አሊ ሲሴይ (ኪሳሚኮስ – ግሪክ)፣ የዓሚ ዱኒያ (ስታንዳርድ ኤፍ ሲ – ሴራሊዮን)

አማካዮች: መሐመድ ሜዶ ካማራ (ኩዌት ኤስ ሲ – ኩዌት)፣ አልፍሬድ ሳንኮህ (አል ጃባሌን – ሳውዲ አረቢያ)፣ ማይክል ላሁውድ (ሲንሲናቲ – አሜሪካ)፣ ጆን ካማራ (ኤፍሲ ካይሳር – ካዛኪስታን)፣ ጁሊየስ ዎባይ (ክለብ የለውም)

አጥቂዎች: ኪይ ካማራ (ቫንኩቨር ዋይትካፕስ – ካናዳ)፣ አልሃሰን ካማራ (ቢኬ ሃከን – ስዊድን)፣ ኢብራሂም ኮንቴህ (ፒኤስአይኤስ – ማሌዥያ)፣ ክዋሜ ክዌ (ቫይኪንጉር – አይስላንድ)፣ መሐመድ ቡያ ቱራይ (ትሩይደን – ቤልጂየም)፣ ሼካ ፎፋና (አል ናስር – ኦማን)፣ አማዱ ባካዮኮ (ኮቨንትሪ ሲቲ – እንግሊዝ)፣ ክርስቲያን ሞስስ (ቪቦርግ – ዴንማርክ)