ወላይታ ድቻ የቀድሞ ግብ ጠባቂውን አስፈርሟል

ወላይታ ድቻ በዝውውር መስኮቱ ሁለተኛ ግብ ጠባቂውን ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል። 

መኳንንት አሸናፊ ወደ ቀድሞ ክለቡ መመለሱ ተረጋግጧል። ግብ ጠባቂው ለድቻ ለመፈረም ከተስማማ ሳምንታት ቢያስቆጥርም ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ወሳኝ ጨዋታዎች የነበሩበት በመሆኑ በይፋ ሳይፈርም ቆይቶ ነበር። መኳንንት በ29ኛ ሳምንት ደቡብ ፖሊስ ወደ ዱራሜ ተጉዞ ሀምበሪቾን በረታበት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዶ የነበረ በመሆኑ ማክሰኞ ለከፍተኛ ሊጉ ዋንጫ ደቡብ ፖሊስ ባህር ዳር ከተማን ሲገጥም የማይሰለፍ ይሆናል። 

መኳንንት ከዚህ ቀደም በወላይታ ድቻ የተጫወተ ሲሆን በ2006 ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የቡድኑ አባል ነበር። በደቡብ ፖሊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ካሳለፈ በኋላም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደቡብ ፖሊስን ጎል ጠብቋል።

በርካታ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ሌላኛው ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነትን ማስፈረሙ የሚታወስ ነው። 

በተያያዘ ዜና ክለቡ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ 3 ተጫዋቾችን ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ደግሞ 7 ተጫዋቾችን ለሙከራ የጠራ ሲሆን በዝግጅት ወቅት በሚያሳዩት አቋም አምስት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን እንደሚያድጉ ታውቋል።