የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ ከሊጉ መጀመር አንድ ሳምንት በፊት ይደረጋል

ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2011

የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከሊጉ መጀመር አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሊጉ እና የዋንጫ አሸናፊው መካከል ይከናወናል።

የ2010 የፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባ ጅፋር እና መስከረም 19 አሸናፊው የሚለየው የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለ ድልን የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ጥቅምት 11 ቀን 2010 በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረግ ይሆናል።

ወጣ ገባ በሆነ መልኩ የሚካሄደው የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በ1977 ከተጀመረ ወዲህ በ10 አጋጣሚዎች ሳይከናወን ሲቀር በአጠቃላይ 26 ጊዜ ተካሂዷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና 5 ፣ ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ይከተላሉ፡፡ አምና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱም አይዘነጋም።

በተያያዘ መረጃ ፈዴሬሽኑ የኢትዮጵያ ኘሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር አፈፃፀም ግምገማ እና የ2011 ዓ.ም የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄድ  አስታውቋል፡፡ ሊጉ ጥቅምት 17 እንደሚጀምር መገለፁም የሚታወስ ነው።