አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ሽረ እንዳስላሴ በራሱ ሜዳ ጨዋታዎችን እንደሚከናውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።
በ2010 የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊግ ሲወዳደር የቆየው ሽረ እንደስላሴ ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ በኋላ በሜዳው የሚደርጋቸውን ጨዋታዎች ለማስተናገድ ወደ መቐለ ይሄዳል ወይስ በራሱ ስታድየም ይቀጥላል የሚለው ጉዳይ እስካሁን የለየለት አልነበረም። በስተመጨረሻ ክለቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሳተፍበት የሀገሪቱ ዋና ሊግ ላይ የሚኖሩትን ጨዋታዎች በሽረ ስታድየም እንደሚከናውን በተለይም ለሶከር ኢትዮጽያ ገልጿል።
በስታድየሙ ጥራት ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሀዱሽ ሜዳው በሳር የተሸፈነ ባይሆንም ጨዋታ ለማከናወን እጅግ በቂ መሆኑን እና ስታድየሙ የተመልካች መቀመጫዎች የተዘጋጁለት ከዛም በተጨማሪ ሁለት የመልበሻ ክፍሎች ፣ ከ8 በላይ የመታጠቢያ ቤቶች እና የህዝብ መፀዳጃ ቤትን ያካተተ ከመሆኑም በላይ አምስት የመግቢያ በሮችም እንዳሉት አስረድተዋል። ስራ አስኪያጁ ጨምረውም የስታድየሙ ቀሪ ግንባታዎች እየተከናውኑ መሆናቸውን እና ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት እንደሚጠናቀቁም ገልፀዋል።
አምና በተመሳሳይ ወደ ሊጉ ያደገው ወልዋሎ ዓ.ዩ በዓዲግራት ይጠቀምበት የነበረው የመጫወቻ ሜዳ ሳር አልባነት በብዙዎች ዘንድ ሲያነጋግር መቆየቱ ይታወስል።