በትግራይ ዋንጫ ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ወልዋሎ እና መቐለ ድል አስመዝግበዋል

ቅዳሜ የተጀመረው የትግራይ ዋንጫ ዛሬም ሲቀጥል ወልዋሎ እና መቐለ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

8:00 ላይ ወልዋሎ እና ሽረ እንዳስላሴን ያገናኘው ጨዋታ በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስም ይሁን ኳስ በመቆጣጠር ወልዋሎዎች ብልጫ ባሳዩበት የመጀመርያው አጋማሽ ተደጋጋሚ የጎል እድሎችንም ፈጥረዋል። አዶንጎ እና አብዱራህማን ባደረጓቸው ሙከራዎች ወደ ሽረ የግብ ክልል መቅረብ የጀመሩት ወልዋሎዎች በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ  በመድረስ ረገድ ስኬታማ ቢሆኑም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ደካማ መሆን በመጀመርያው አጋማሽ ጎል እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። በተለይም አብዱልራሕማን ከመስመር አሻግሯት ፕሪንስ በግንባሩ ገጭቶ ያመከናት በወልዋሎ በኩል የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች።

በዋነኝነት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በማግኘት ላይ የተመሰረተው የሽረ እንዳስላሴ አጨዋወት ደግሞ በተጋጣሚው ቡድን ወልዋሎ በቶሎ ተገማች መሆኑ ኳስ ለመመስረት እንዲቸገር ቢያደርገውም ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ የሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ ነበር። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ግብ ጠባቂው ሃፍቶም ቢሰጠኝ ያሳየው እንቅስቃሴ ማየት በቂ ነው። በጣም ተቀራርበው እና ለተከላካዮቻቸው እጅግ ተጠግተው በሚጫወቱ የመሃል ሜዳ ተሰላፊዎች የተዋቀረው ሽረ የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ያሳየው አዝማሚያ አናሳ መሆን ቡድኑ በቁጥር ትንሽ ሙከራዎች ብቻ እንዲያረግ ከማድረጉም ባለፈ በአጥቂ መስመር የተሰለፈው ሰዒድ ሁሴን ከቡድኑ እንዲነጠል አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪም የቡድኑ የኳስ አመሰራረት ሂደት በአንድ አቅጣጫ (ክብሮም ብርሃነ እና ሄኖክ ብርሃኑ) የተንጠለጠለ መሆኑ በወልዋሎዎች በኩል ተገማች አድርጎታል።

በመጀመርያው አጋማሽ አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያረጉት ሽረዎች በአምበሉ ሙሉጌታ ዓንዶም ሁለት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ተጫዋቹ ከርቀት አክርሮ መቷት ከመረቡ በላይ የወጣችው ኳስ በመጀመርያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች። በወልዋሎ በኩልም የመጀመረውያው አጋማሽ ሊያልቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገው ነበር። እንየው ካሳሁን አሻምቷት ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት የነበረው አዶንጎ መቶ ያመከናትም ሙከራ ትጠቀሳለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው የተሻለ የጨዋታ ፍሰት የታየበት ሲሆን ወልዋሎዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በቁጥር ያነሰ የጎል ሙከራ ያደረጉበት ፤ ሽረዎች ደግሞ ከመጀመርያው አጋማሽ ድክመታቸው ተሻሽለው መቅረብ የቻሉበት ነበር። ጨዋታው በተጀመረ 10 ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በርከት ያሉ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉት ሽረዎች በተለይም ሙሉጌታ ዓንዶም ከማዕዘን አሻምቶት ጅላሎ ሻፊ በግንባሩ ገጭቶ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡት እና ሰዒድ ሁሴን በጥሩ ሁኔታ ይዞ የገባውን ኳስ መትቶ ብርሃኑ ቦጋለ ያወጣው እንዲሁም ደሳለኝ ደባሽ ከርቀት መትቶ በረከት አማረ ያዳነበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። 

በፈጣን ከመከላከል የማጥቃት ሽግግር ጎል ለማግኘት በተንቀሳቀሱት ወልዋሎዎች በኩህ አዶንጎ አሻምቶት አማኑኤል ጎበና በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት በ57ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ  በአብዱራሕማን ፉሴይኒ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት ሪችሞንድ አዶንጎ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኋላም ጎል ፍለጋቸው የቀጠሉት ወልዋሎዎች ብዙም ሳይቆዩ እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም ፕሪንስ ከመስመር በኩል ያሻማው ኳስ አዶንጎ በማይታመን መልኩ የሳታት ተጠቃሽ ናት። 

ሽረዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሄኖክ ብርሃኑን በዘላለም በረከት ቀይረው የተከላካይ ቁጥራቸው በመቀነስ ጎል ፍለጋ አጥቅተው ቢጫወቱም  ጎል እና መረብ ማገናኘት ተስኗቸው ጨዋታው በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በ10:00 በተጀመረው የአክሱም እና የመቐለ ጨዋታ ሙከራዎች ባይበራከቱበትም ማራኪ እና ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነበር። ከባለፈው ጨዋታ በተለየ ብዙ ለውጦች አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት መቐለዎች ወጣቱ አሸናፊ ሃፍቱምን ጨምሮ በርከት ያሉ አዳዲስ ፊቶች በመጀመርያው አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል።

በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ መቐለዎች ተሽለው በታዩበት የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጎል ለማግኘት የፈጀባቸው 4 ደቂቃ ብቻ ነበር። በዚህም ዮናስ ግርማይ ከማዕዝን የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በ4-4-2 ከተፈጥሯዊ አማካይ ተከላካይ ውጪ ወደ ሜዳ የገቡት መቐለ ከተማዎች ኳስ በሚመሰርቱበት ወቅት በአማካይ ቦታ የጎንዮሽ የመቀባበያ አማራጭ የመፍጠር ሃላፊነት የነበረባቸው ዮናስ ገረመው እና እንዳለ ከበድ እጅግ በተለጠጠ አቋቋም መጫወታቸው በመሀል አማካይነት የተሰለፉት ሃይለአብ ሃይለሳላሴ እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ሰፊ የጎንዮሽ ክፍተት እንዲሸፍኑ አድርጓቸው ነበር።

በጨዋታው ሳይጠበቅ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረጉት አክሱም ከተማዎችም በርከት ያሉ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም በጨዋታው ኮከብ ሆኖ ያመሸው ልዑልሰገድ አስፍው በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ለጎል የቀረቡ ነበሩ። ተጨዋቹ ከርቀት አክርሮ መቶ ሶፈንያስ ሰይፈ ያዳናት ሙከራ ተጠቃሽ ናት። አክሱሞች ከነዚህ ሙከራዎች በኋላ ጎል ያገኙ ሲሆን በ27ኛው ደቂቃ ላይ ስለሺ ዘሪሁን ከጎሉ ፊት ለፊት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በመቐለ በኩልም እንዳለ ከበደ ከመዕዘን አሻምቶ ኦሰይ ማውሊ ያልተጠቀመባት እና ዮናስ ገረመው ከርቀት መቶ ጅቤድ ዑመድ ያዳነበት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።


በሁለተኛው አጋማሽ መቐለ ከተማዎች በርካታ ቅያሬዎችን አድርገው ሜዳ ሲገቡ አክሱሞች በተቃራውኒ የመጀመርያው አጋማሽ አሰላለፋቸውን ሳይለውጡ ተመልሰዋል። ሚዛኑ በተወሰነ መልኩ ወደ መቐለ ባጋደለበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መቐለ ከተማዎች ጎል ለማስቆጠር የፈጀባቸው ደቂቃ ጥቂት ነበር። በሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ያሬድ ከበደ አንድ ሁለት ተቀባብለው ሳሙኤል መሬት ለመሬት አክርሮ  በመምታት ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች መቐለዎች  ጠንክረው  የታዩ ሲሆን ባሳደሩት ጫና ምክንያትም አክሱሞች ትኩረታቸው መከላከል ላይ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። መቐለዎች ካደረጓቸው ሙከራዎችም በአንዱም ጋብርኤል መሃመድ ከመሃል ሜዳ ያሻገረው ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ኦሰይ ማውሊ ቢያገኘውም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በጨዋታው ብዙ የጎል ዕድሎች ያመከነው አጥቂው ብዙም ሳይቆይ በተመሳሳይ አቋቋም ላይ ሆኖ ኳስ ከመሀል ሜዳ ተሻግሮለት ጅቤድ ዑመድ ጋር አንድ ለ አንድ ቢገናኝም እሱንም በተመሳሳይ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከዚህ በተጨማሪ ያሬድ ሃሰን አሻምቶት ሳሙኤል ሳሊሶ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበትም ተጠቃሽ ሙከራ ነው። የተከላካይ መስመራቸው ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው ለመጫወት የሞከሩት መቐለ ከተማዎች አጨዋወቱ ቡድኑ ኳስ በሚያጣበት ሰዓት ብዙ ጉልበት እንዳያባክን እና ተጋጣሚን በደንብ እንዲያፍን ያገዘ ቢሆንም ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ግን የረጃጅም ኳሶች ሰለባ እንዲሆን አድርጎታል። በተለይም ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች አሚኑ እና ቢያድግልኝ ቶሎ የመከላከል ቅርፃቸው የመያዝ ችግር ይስተዋልባቸው ነበር። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት መዋእል ቀፀላ እና ልዑልሰገድ አእስፋው ያደረጓቸው ሙከራዎች ናቸው። በተለይም ልዑልሰገድ ክፍተቱን ተጠቅሞ አክርሮ መቶ ሶፈንያስ ሰይፈ በሚያስደንቅ ሁኔታ መልሶት ብረት ገጭቶ የተመለሰው ሙከራ ተጠቃሽ ነው።

ሆኖም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም ብልጫ የነበራቸው መቐለ ከተማዎች ያሬድ ከበደ በቀድሞ ክለቡ ላይ ያስቆጠረውን ጎል አክለው አክሱምን 3 ለ 1 አሸንፈው ወጥተዋል።