ሪፖርት | የጣና ሞገዶች እና ሰጎኖቹ ድል አድርገዋል

ሪፖርት | የጣና ሞገዶች እና ሰጎኖቹ ድል አድርገዋል

በ14ኛው የጣና ደርቢ ባህር ዳር ከተማዎች ፋሲል ከነማን 2ለዐ በመርታት ደረጃቸውን ሲያሻሽሉ ነጌሌ አርሲዎች ከመመራት ተነስተው ወልዋሎን 2-1 በማሸነፍ ከአራት ሳምንታት በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ

በአዳማ የተደረገው ቀዳሚው ጨዋታ በጣና ደርቢ ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ ፋሲል ከነማን ከባህር ዳር ከተማ አገናኝቷል። ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅሰቃሴ በማስመልከት የተጀመረው ጨዋታው የኋላ ኋላ የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ዐፄዎቹን ብልጫ እንዲወስዱ አስችሏቸዋል። ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ያሻገረውን ኳስ ታምራት ኢያሱ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ለግብ ጠባቂው ያሳቀፈበት፣ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ናትናኤል በግንባሩ ገጭቶ አድርጎ መይስ ፖይቴ የተጠቆጣጠረበት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲጠቀስ የጣና ሞገዶች መሳይ አገኘው በመስመር በኩል ይዞ ገብቶ በጠባብ አንግል መትቶ አደጋ ሳይፈጥር ከቀረው ሙከራ ውጪ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስመለክቱን አጋማሹ ተገባዷል።

ዐፄዎቹ ወደፊት በመሄድ የተሻሉ መስለው በተመለሱበት በሁለተኛ አጋማሽ ክፍት የግብ አድል ፈጥረው ከጨዋታ ውጪ ተብሎባቸው የጣና ሞገዶች ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶ ቶሎ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ ኳሱን በመጣል ሳይጠበቅ የመጀመሪያ ግብ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፤ 47ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው በረጅሙ የጣለውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል አግኝቶ ግብ ጠባቂው መውጣቱን ተመልክቶ ከፍ አድርጎ በመምታት ድንቅ ግብ መረብ ላይ አሳርፏል።

የጣና ሞገዶች ከግቡ መቆጠር በኋላም በተደጋጋሚ ወደፊት ሄደው ተጨማሪ ግብ የሚሆኑ አጋጣሚዎችንም ፈጥረዋል፤ በቆመ ኳስ ፍፁም ፍትህአለው አድርጎት ሞይስ ፖይቴ እንዴትም ጨርፎ ያወጣባቸው ሙከራ መሪነታቸውን ለማጠናከር የተቃረበ ሲሆን 69ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። አደም አባስ እና ብሩክ ሰሙ ተቀባብለው ገብተው ብሩክ ሰሙ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ በግሩም አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎ መሪነታቸውን አጠናክሯል። ዐፄዎቹም ጫን ብለው በመግባት ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት ፊት መስመር ላይ በሚታይ አጨራረስ ችግር ሳይጠቀሙ እየቀሩ 14ኛው የጣና ደርቢ በባህርዳር ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ነጌሌ አርሲ

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲን ከነጌሌ አርሲ ያገናኘ ሲሆን ቡድኖቹ ዘለግ ላለ ደቂቃ ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የግብ ማግባት ሙከራም ሆነ ወደፊት ሄደው እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ሆኖም ግን የተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል በመድረስ አኳያ ሰጎኖቹ የተሻሉ የነበረ ቢሆንም ቢጫ ለባሾቹ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል፤ 39ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ መሃል ለመሃል ያሻገረለትን ኳስ ስምዖን ማሩ አግኝቶ በጥሩ አጨራረስ ኳስና መረብ አገናኝቷል።

ወደ ጨዋታ ለመመለስ ከግቡ መቆጠር በኋለ የተነቃቁት ሰጎኖቹ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ገብረመስቀል ዱባለ በግንባሩ ገጭቶ አድርጎ ከአግዳሚው ለጥቂት ከፍ ብሎ ካለፈባቸው እና የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ የአቻነት ግብ በኪቲካ ጅማ አማካኝነት አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ከተሻረባቸው በኋላ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል፤ ሮሆቦት ሰላሎ የቆመ ኳስ አክርሮ መትቶ ተጨርፎ ስሻገር የቢጫ ለባሾቹ ተከላካዮች ”ከጨዋታ ውጪ ነው” ብለው ሲዘናጉ ሳጥን ውስጥ የነበረው ገብረመስቀል ዱባለ ሾልኮ በመውጣት አስቆጥሮ አቻ ሆኖ ለእረፍት ገብተዋል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ተመልሶ የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረው የተነቃቁት ሰጎኖቹ ካቆሙበት ጥንካሬያቸውን አስቀጥለው መሪነቱን ለመረከብ በሚያደርጉት ፈጣን ማጥቃት እንቅስቃሴ ተጋጣሚዎቻቸውን እየፈተኑ ቆይተው 56ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ቦና ቦካ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኪቲካ ጅማ  በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ መሪነቱን እንዲረከቡ አስችሏቸዋል።

ሰጎኖቹ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ከግቡ በኋላ ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም ደቂቃው በሄደ ቁጥር ቢጫ ለባሾቹ ጫና በማሳደራቸው የነሱን ጥቃት መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው ሰንብተዋል። ቢጫ ለባሾቹም ቢያንስ አቻ ለመሆን በሙሉ ኃይላቸው እየገቡ በተለየም 70ኛው ደቂቃ ላይ አፈወርቅ ከሳጥኑ ጠርዝ አድርጎ ለጥቂት ከፍ ያለበት አጋጣሚ አቻ ሊያደረሰጋቸው የቀረበ ቢሆንም  በመጨረሻም የነጌሌዎች መከላከል ተሳክቶላቸው ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ ድል ተመልሰው ጨዋታው ተቋጭቷል።