ቀይ ቀበሮዎች ከ22 ዓመታት በኋላ የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ከአምስት ቀናት በኋላ ይጀመራል።

ቀይ ቀበሮዎቹ የሚሳተፉበትና በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የ2026 ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ሊጀመር የአምስት ቀናት ዕድሜ ቀርተውታል። አስተናጋጇ ሀገር እና የወቅቱ ቻምፕዮን ሞሮኮ፣ ግብፅ እና ቱኒዝያ በሚገኙበት ምድብ 1 የተደለደለው ብሔራዊ ቡድናችን ግንቦት 5 ግብፅን በመግጠም ውድድሩን የሚጀምር ሲሆን በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ደግሞ ግንቦት 8 ከአስተናጋጅዋ ሞሮኮ ጋር ተጫውቶ ግንቦት 11 ከቱኒዝያ ጋር ይጫወታል። ከ22 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስቱም የምድብ ጨዋታዎቹ በሰሜናዊ ምዕራብ ሞሮኮ በምትገኘው ሴይል ከተማ በሚገኘው መሐመድ 6ኛ የእግር ኳስ ኮምፕሌክስ የሚያከናውን ይሆናል።
አስራ ስድስት ቡድኖች በአራት ምድቦች ተከፍለው
የሚያደርጉት ይህ ውድድር ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 25 በመሐመድ 6ኛ የእግር ኳስ ኮምፕሌክስ እና ኤል ሀሰን ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን ከእያንዳንዱ ምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁ ቡድኖችም ወደ ሩብ ፍፃሜው ከመሻገር ባለፈ በቀጥታ በ2026 የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ይሆናል።
በተጨማሪም ከምድባቸው ሶስተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ቡድኖች የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አድርገው የጥሎ ማለፉ አሸናፊ ሁለት ቡድኖች እና ቀድመው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ስምንት የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚዎች በድምሩ አስር ሀገራት በኳታር አዘጋጅነት ወደ የሚካሄደውና አርባ ስምንት ሀገራት ወደ የሚካፈሉበት የ2026 የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የሚያመሩ ይሆናል።

