ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲሱ መርሐግብር ላይጫወት እንደሚችል ፌዴሬሽኑን አስጠንቅቋል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲሱ መርሐግብር ላይጫወት እንደሚችል ፌዴሬሽኑን አስጠንቅቋል

ንግድ ባንክ እጅግ ወሳኝ ወደሆነ ምዕራፍ በደረሰው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ የመርሐግብር ለውጥ መደረጉን ሲቃወም በአዲሱ መርሐግብር ላይጫወት እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

የ2018 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። አንጋፋው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ክስተቱ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በግብ ልዩነት ተበላልጠው 1ኛ እና 2ኛ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በ25ኛ ሳምንት ደግሞ እርስበርስ ይገናኛሉ።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ምክንያቱን በይፋ ሳያሳውቅ ይህ ጨዋታ የውድድሩ መዝጊያ እንዲሆን ባሰበ መልኩ የ25ኛ እና 26ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ፕሮግራም ቀያይሮ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀድመው እንዲካሄዱ ትናንት ምሽት አሳውቋል።

በዚህም ምክንያት ማክሰኞ 4 ሰዓት ሲል ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ጋር አበበ ቢቂላ ላይ ፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በተመሳሳይ ሰዓት እንዲጫወቱ ፌዴሬሽኑ አዟል።

በውሳኔው ቅሬታ የተሰማው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቅሬታ የማመልከቻ ደብዳቤ ልኳል።

በደብዳቤው ላይ “ከስልጠና ሳይንስም ሆነ ከስፖርት ሕግ አስተዳደር አንጻር የእግርኳሱን ፍትሐዊነት የሚጎዳ” እንዲሁም “ከጨዋታ ታክቲክም ሆነ ከተጫዋቾች የሰው ኃይል አጠቃቀም ጋር ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን በመረዳት ቀደም ብሎ በወጣው መርሐግብር ብቻ ለመሳተፍ እንዲወሰንለት” በሚጠይቅ ይዘት የገለጸው ንግድ ባንክ ከዚህ ውጪ በወጣ መርሐግብር ላይሳተፍ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ንግድ ባንክ አክሎም

“ውድድሩን ለማጠናቀቅ ግልፅ ምከንያት እና የኘሮግራሙ አላማ በተጨባጭ ባልተቀመጠበት በድፍኑ በደንቡ ላይ ኘሮግራሙ ተቀይሯል ተጫወቱ መባሉ አሳማኝ ሆኖ አላገኘነውም። ምንም እንኳን አወዳዳሪው አካል የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ እንደአስፈላጊነቱ የኘሮግራም ማሻሻያ ሊያደርግ ይችላል ቢልም ቀን፣ ስዓትና ቦታ እንጂ የተጋጣሚ ቡድኖችን ማንነት በዕጣ አና በቀደመ የውጤት ደረጃ የተወሰነ በመሆኑ በደረጃ 1ኛ አና 2ኛ ላይ ያሉ ቡድኖችን ትኩረት በሰጠ መልከ ኘሮግራሙን በእጅጉ በሚያፋልሰው መልኩ መቀያየሩ የኘሪሚየር ሊጉን የውድድር አመራርም ሆነ የአለም አቀፍ እግር ኳስ ውድድር አመራርን የሚጥስ በመሆኑ ሁለቱ ቡድኖች እድላቸውን በራሳቸው የእርስ በርስ ጨዋታ የሚወስኑበት እድል ከፊት ለፊታቸው ተቀምጦ ቀድሞ ባልተቀመጠ የውድድር ኘሮግራም ማሻሻያ ተደርጓል ተጫወቱ በሚል የተገለፀውን የስፖርት ማህበሩ ባለድርሻ አካላት ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት አወዳዳሪው አካል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚመስል መልኩ ታሪክ ቀያሪ ውሣኔ ለመወሰን የተገደደበትና የተነሳበትን ምክንያት በሕግ እና በሞራል አግባብ አሳማኝ ሆኖ ማግኘት ባለመቻላችን የውድድሩን ፍትሐዊነት በወጣው የቡድኖች የሳምንታት ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ ማን ለየትኛው መልቀቅ እንደሚችል በማይወሰንበት ሁኔታ የሁለቱ ቡድኖች ውጤት እርስ በርሳቸው ሲገናኙ እና ቀሪ ጨዋታቻውን በሚያስተዳድሩበት አግባብ እንዲወሰን አየጠየቅን ይህ የማይፈፀም ከሆነ ፌዴሬሽኑ ከውድድሩ አስቀድሞ የጋራ የውይይት መድረከ አንዲያዘጋጅልን አንጠይቃለን፡፡”

ሲል በደብዳቤው ገልጿል።