” የአቻ ውጤቱ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ ” የኬንያ አሰልጣኝ ሴባስቲየን ሚኜ

ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የማጣርያ ጨዋታ ወደ ባህር ዳር ያመራወሰ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ያለ ጎል አቻ በመለያየት ነጥበ ተጋርቶ ወጥቷል። ከጨዋታው በኋላ የኬንያው አሰልጣኝ ሴባስቲየን ሚኜ ለጋዜጠኞች ከሰጡት መግለጫ ዋና ወመናዎቹን ሀሳቦች ጠቅልለን አቅርበነዋል።

” በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ እድሎችን መፍጠር  ችለን ነበር። ከዛ በኋላ ግን ከብዶን ነበር። ምክንያቱም ከአስራ ሁለት ተጫዋቾች ጋር ነበር የተጫወትነው። የማወራው ስለ ዳኛው ሳይሆን ስለ ደጋፊዎች ነው። የነበረው የደጋፊ ድባብ ለኛ ከባድ ነበር። የሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ለውጦችን በማድረግ ለማሸነፍ የሚያስችለን አጋጣሚ ፈጥረን ነበር። እናም ጥሩ ነበርን። ነገር ግን የግራ ተከላካያችን ከተጎዳ በኋላ ደጋፊዎች እና የተጋጣሚያችን ጫና ነገሮችን አክብዶብን ነበር። 

” በጨዋታው ጥሩ አጋጣሚዎች ፈጥረናል። በእኛም በኢትዮጵያም በኩል የፍፁም ቅጣት ምት ቅሬታዎች ነበሩ። በአጠቃላይ የአቻ ውጤቱ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ። ከአራት ቀን በኋላ በሜዳችን ለማሸነፍ እንሞክራለን። በእርግጠኝነት ልናገር የምችለው በኢትዮጵያ እና በእኛ መካከል የሚደረገው ጨዋታ የፍፃሜ ጨዋታ ያህል ይሆናል። “