ቅዱስ ጊዮርጊስ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂን ለማስፈረም ተስማምቷል

ላለፉት ሰባት ዓመታት በሮበርት ኡዶንካራ ግቡን ሲያስጠብቅ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በክረምቱ ከዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ጋር ከተለያየ በኋላ ሌላ የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። 

ሁለት ግብ ጠባቂዎችን ለሙከራ አምጥቶ ለአንድ ወር ያህል ከቡድኑ ጋር ሲሰሩ ቢቆዩም አመርቂ እንቅስቃሴን ባለማሳየታቸው በማሰናበት ሌላ ግብ ጠባቂ ሲያፈላልግ ቆይቶ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ግብ ጠባቂ የሆነው ፓትሪክ ማታሲን ለማስፈረም ከስምምነት መድረሱ ታውቋል። የ30 አመቱ ግብ ጠባቂ ትላንት ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በባህር ዳር ስታዲየም ባደረጉት እና ያለ ግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ ሙሉ ደቂቃውን ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በጉዳዩ ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ወደ ቅደስ ጊዮርጊስ ለመግባት ስምምነት እንዳደረገ ተናግሯል። “ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስምህ ተያያዘ ያላችሁኝ ነገር እውነት ነው። ከክለቡ ጋር ድርድር አድርጌ ለክለቡ ለመፈረም ተስማምቻለሁ፤ እነሱም ወደ ቡድኑ ገብቼ እንድቀላቀል ፍላጎት አላቸው። አሁን ላይ ለሀገሬ ከኢትዮጵያ ጋር የመልስ ጨዋታ እናደርጋለን። የእሁዱን ማጣሪያ ጨዋታውን ከጨረስኩ እና ከክለቤ ተስካር መልቀቂያዬን ከወሰድኩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እጫወታለው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ።” ሲል ገልጿል።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የሆነው ንዲዝዬ ኤሚ ተጫዋቹን በባህር ዳር ተገኝቶ የተከታተለው ሲሆን በ10 ቀናት ውስጥ በይፋ የቅዱስ ጊዮርጊስ ንብረት ይሆናል ተብሏል። 

እግር ኳስን በኬንያው ካባራስ ዩናይትድ የጀመረው ፓትሪክ በሌላኛው የኬንያ ቡድን ኤ ኤፍሲ ሊዮፓርድስ፣ ተስካር እንዲሁም በፖስት ሬንጀርስ ተጫውቷል። ከ2017 ጀምሮ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ግብ ጠባቂ በመሆን እየተጫወተም ይገኛል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1997 የውድድር ዓመት ወዲህ እምነቱን በውጪ ግብ ጠባቂዎች ላይ ጥሎ ቆይቷል። ዩጋንዳዊያኑ ካሲቡላ ሀኒንግተን፣ ዴኒስ ኦኒያንጎ እና ሮበርት ኦዶንካራ፣ ቡሩንዲያዊው ንዴዚዬ ኤሚ፣ ታንዛንያዊው ኢቮ ማፑንዳ እና ሰርቢያዊው ዜሊጅኮ ኡዝሚች ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወቱ የውጪ ግብ ጠባቂዎች ናቸው።