መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ በቅቷል፡፡ በ2006 ወደተሳተፈበት ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመመለስም የ90 ደቂቃ ፍልሚያ ቀርቶታል፡፡
የመከላከያው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰዳቸው የድሉ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ሁለታችንም ጋር ለማሸነፍ የነበረው ጥረት ከፍተኛ ነበር፡፡ ከተሸነፍክ መውደቅህ ስለማይቀርና ወደ ፍፃሜ ለማለፍ የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ ከባድ ጉልበት የሚፈልግ ነበር፡፡ ሜዳውም ኳስ ይዞ ለመጫወት ምቹ አልነበረም፡፡
‹‹ የመጀመርያው 45 ላይ ጊዮርጊሶች ጠንከር ብለው ቀርበዋል፡፡ በ2ኛው አጋማሽ ግን ክፍተቶቻችንን አስተካክለን ወደ ሜዳ ገብተናል፡፡ ጨዋታውን ተቆጣጠረን በመጫወታችን ማሸነፋችን ይገባናል፡፡
ለማሸነፋችን በኳስ ቁጥጥር መብለጣችን ወሳኝ ነበር፡፡ ኳስ በምንይዝበት ጊዜ በፍጥነት ወደ ማጥቃት ወረዳው ለመግባት መጣራችን ለውጤት አብቅቶናል፡፡ ››
የተሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማን በበኩላቸው የአዲስ የውድድር ዘመን መጀመርያ በመሆኑ ውጤቱ የሚያስገርም እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ በውጤቱ አልተገረምኩም፡፡ ምክንያቱም አዲስ የውድድር ዘመን ነው የጀመርነው፡፡ ለ4 ሳምንት ከባድ ልምምድ ስለሰራን ጉልበታችንን አሟጠናል፡፡ ለማገገምም ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡
‹‹ በእርግጥ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት አያስደስትም፡፡ ነገር ግን ዛሬ ብንሸነፍም በጥሩ መንገድ ላይ እየተጓዝን እንደሆነ ለተጫዋቾቼ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ በዘረጋነው ሲስተም ላይም እምነት አለን፡፡ ትኩረታችንም በፕሪሚየር ሊጉ እና ቻምፒዮንስ ሊጉ ላይ ጥሩ ውጤት ማምጣት ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡
በእለቱ 2ኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከነማ በበረከት ይስሃቅ ብቸኛ ግብ ታግዞ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ ለፍፃሜው አልፏል፡፡
ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በ2ኛው አጋማሽ የተሸሉ ስለነበሩ እንዳሸነፉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ጨዋታው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ እንደመሆኑ ከባድ ነበር፡፡ የነጥብ ጨዋታዎች ባለማድረጋችን የቡድኔን አቋም ማወቅም አልችልም፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ አልቻልም፡ በ2ኛው አጋማሽ ግን የተሻለ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ብልጫ የወሰድን ሲሆን የግብ እድሎችም ፈጥረናል፡፡ በመጨረሻም ግብ አስቆጥረን አሸንፈን ወጥተናል፡፡
የድቻው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው ያገኙትን እድል በአግባቡ ባለመጠቀማቸው እንደተሸነፉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ሀዋሳዎች ከኛ በተሻለ ተጭነው ተጫውተዋል፡፡ ቁጥራችንን አብዝተን በጥንቃቄ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር ያሰብነው፡፡ በዚህም በተለይ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የግብ እድል ብንፈጥርም አልተሳካልንም፡፡ እነሱ ደግሞ ያገኙትን የግብ እድል ተጠቅመው አሸንፈው ወጥተዋል፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡