የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ እና የጥሎ ማለፍ አሸናፊ የሚገናኙበት የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ መስከረም 19 ይካሄዳል ቢባልም በእለቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቦትስዋና አቻው ጋር በጋቦሮኒ የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርግ በመሆኑ ጨዋታው በተያዘለት ቀን የመደረጉ ሁኔታ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የውድድር እና ስነስርአት ኮሚቴ ጨዋታው መስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም እንደሚካሄድ መረጃ ቢልክም የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ የደረሱት መከላከያ እና ሀዋሳ ከነማ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን በማስመረጣቸውና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በግማሽ ፍፃሜ የሚመለከቷቸው ተጫዋቾች ካሉ እንደሚያካትቱ መናገራቸውን ተከትሎ ጨዋታው ሊራዘም አልያም እንደባለፈው የውድድር ዘመን ሊሰረዝ ይችላ፡፡
በፌዴሬሽኑ ደንብ መሰረት አንድ ክለብ 3 እና ከዛ በላይ ተጫዋች ካስመረጠ የውስጥ ውድድር የማድረግ ግዴታ የለበትም፡፡
ይህ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ አምና በደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል መደረግ ቢኖርበትም ሳይካሄድ መዘለሉ የሚታወስ ነው፡፡
በተያያዘ የኢትዮጵያ ሴቶች አሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ መቼ እንደሚካሄድ አልተወሰነም፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በጥሎ ማለፉ ባለድል ደደቢት መካከል የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ሊካሄድ የታሰበው ባለፈው አመት ቢሆንም ለዘንድሮ አመት መሸጋገሩ የሚታወስ ነው፡፡