“የሚድን ሰው የለም…” አቶ አብነት ገብረመስቀል

በ2010 የውድድር ዘመን አንድም ተጠቃሽ ዋንጫ ያላሳካውና ከ2006 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ መድረክ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የማይሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በቢሸፍቱ ከተማ ባስገነባው የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ወጣቶች አካዳሚ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ትላንት ረፋድ ላይ ቡድኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እያደረገ ባለበት ወቅት በስፍራው ከተገኙት የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገ/መስቀል ስለክለቡ ያለፈው ዓመት የውድውር ጉዞ፤ ስለ ቀጣይ ዕቅዱ እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከዳንኤል መስፍን ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል። 


የክለቡ የሁልጊዜ እቅድ በአፍሪካ መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን በመስራት ረጅም ርቀት እንዲጓዝ ማድረግ እንደሆነ በንግግሮዎ እንሰማለን፡፡ ዘንድሮ ባልተለመደ ሁኔታ በየትኛውም የአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ተሳታፊ አይደለም። ክለቡ ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድነው ብሎ ራሱን ፈትሿል ?

በአጠቃላይ ይህ እግርኳስ ነው። እግርኳስ ደግሞ በውስጡ ይዟቸው የሚመጡ በርካታ ነገሮች አሉ። ዘንድሮ ያልጠበቅናቸው ነገሮች ነበሩ፤ ይህንንም በዝርዝር አይተናል፡፡ በመጀመርያ የተጫዋቾች ጉዳት አንዱ ምክንያት ነው። በተለይ በአጥቂ ስፍራ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድን ሄደው ሲመለሱ የረጅም ጊዜ ጉዳት ማስተናገዳቸውና በፍጥነት ማገገም አለመቻላቸው ቡድኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው። ሁለተኛ የራሳችን ችግር የምንላቸው ጉዳዮች፤ ለምሳሌ የአሰልጣኞች አቅም፣ የተጫዋችች የአቋም መውረድ እና ለጨዋታዎች በቂ የአዕምሮ ዝግጅት አለማድረግ፤ በተጨማሪም በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት በቂ የሆነ ዝግጅት አለማድረግ ናቸው። በሦስተኛ ደረጃ በውስጣችንም የነበሩ የዲሲፕሊን ችግሮች ነበሩብን፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ ሲደማመሩ በ2010 ጥሩ የውድድር ዓመት አላሳለፍንም። ይህ ደግሞ በሚገባ የታየ ነገር ስለሆነ ምክንያት መደደርደር አያስፈልግም። 

ከዚህ ተነስተን ወዴት ነው የምንሄደው ስንል፤ ተጫዋቾች ላይ ከዚህ ችግር በፊትም በኋላም የወሰድናቸው በቀጣይም የምንወስዳቸው እርምጃዎች ነበሩ፡፡ አንዳንዱን አድርገናል ። ክፍተቶቻችንን ለማረም የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይመጥናሉ የምንላቸውን ከየቦታው መርጠን አምጥተናል፤ እነሱም በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ናቸው፡፡ ሆኖም መጥተው ከቡድኑ ጋር እስኪቀናጁ ድረስ ጊዜ መውሰዱ ችግራችን ቢሆንም ምክንያት ማቅረብ አንፈልግም፤ በመጡ ሰዓት ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ለማቀናጀት እንሞክራለን። ሌላው አሰልጣኙን በኩል ያለውን በደንብ እያየን፣ እየገመገምን፣ እየፈተሽን ነው፡፡ ዘንድሮ የሚቀር የማይፈተሽ ነገር የለም። የተሻለ ነገር ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን።

በእግርኳስ ውስጥ እንግዲህ ትልቅ ቡድን ሆነህ ደጋፊውም ሌላውም የሚጠብቀው በለመድከው ደረጃ እንድትቆይ ነው። ግን አንዳንዴ ደግሞ ከአቅም በላይ በሆኑ ነገሮች እና ደስ በማይሉ ምክንያቶች ደረጃህን የምትሰጥበት መንገድ አለ፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው ውድድር ወደ መጨረሻው አካባቢ ብዙ ተፎካካሪዎች ቢኖሩም እየተላቀቁ የመጡት ነገር ደስ አይልም። ክለቦችም የራሳቸውን ክብር ሸጠው ስታይ እግርኳሳችን የት ደረጃ ላይ እንደደረሰ የተመለከትንበት ስለነበር ያሳዝናል። ይህን ደግሞ ተመርጦ የመጣው አዲሱ ፌዴሬሽንም ቢሆን ችግሩን ለመቆጣጠር እና ለመወሰን ፊቱን አዙሮ ስለነበር ይሄ መስተካከል አልቻለም። በዚህ ምንም ማድረግ አልቻልንም፤ ይህ ሁኔታ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ የሀገራችን እግርኳስ በቀጥታ ገደል ነው የሚገባው። ይህ ሁሉ መዋዕለ ንዋይ በእግርኳሱ እየፈሰሰ መላቀቁ የሚቀጥል ከሆነ ከባድ ነው። ስለዚህ አሰራሩ፣ የነጥብ አሰጣጡ፣ የቅጣት ውሳኔዎቹ  መቀየር አለባቸው። ወደ ውድድር ከመግባታችን በፊት ክለቦችን ሰብስቦ ፌዴሬሽኑ ማናገር አለበት እንጂ ጉዳዮች (ችግሮች) በመጡ ቁጥር ለአንዱ የሚሰጠው ውሳኔ እና ለሌላው የሚሰጠው ውሳኔ የተለያየ ከሆነ ፍታሀዊነት ይኖራል ብዬ አላስብም ።


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከተስፋ ቡድን አድገው ክለቡን በቋሚነት የሚያገለግሉ ልጆች እየወጡ አይደለም፡፡ ችግሩ ምን ላይ ነው? ምልመላ? አሰለጣጠን? ወይስ የተጫዋቾች አቅም? ይሄን ክለቡ ለማስተካከል እየፈተሸው ይገኛል? 

አዎ እንገመግማለን፡፡ በተቻለ መጠን ወጣቶችን ለማሳደግ እንጥራለን። ሆኖም ወጣቶች በጣም ችኩሎች ናቸው፡፡ እድሜያቸውን እና ደረጃቸውን ጠብቀው ለማደግ ብዙዎቹ ፍላጎት የላቸውም። ይህ ትልቅ ክለብ ነው፤ በአንድ ጊዜ ማደግ እና በፍጥነት ለዋናው ቡድን መጫወት ላይኖር ይችላል፤ ትዕግስት ጊዜ ይፈልጋል። ይህን የተመለከቱ አንዳንድ ክለቦች ታዳጊዎቻችንን ጎትቶ ለመውሰድ አይተኙም። ገና ዋናው ቡድን ልምምድ ጀመሩ ሲባል ፍላጎት ማሳየት ይጀመራሉ፤ ይህን ውጣ ውረድ እየተቋቋምን ነው ያለነው። ተጫዋቹ የፈለገበት ተዟዙሮ የመጫወት መብቱን የምናከብር ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ትልቆቹም ትንሾቹም ለመጫወት ልዩ ፍቅር አላቸው። ያ ብቻ ነው ጊዮርጊስ ውስጥ የሚያቆያቸው። ለተጨዋቾችም የምንከፍለው ክፍያ በሊጉ ካሉ ሌሎቹ ክለቦች አንፃር ቢታይ በአራተኛ ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው። ስማችን ትልቅ ነው፤ ግን ክፍያው ትንሽ ነው። ተጨዋቾች ጊዮርጊስ ጋር የሚመጡት ለፍቅር ብለው ነው። በአጠቃላይ ተስፋ ቡድኑን የምንፈትሸው ቢሆንም ከታች የሚመጡት ተጫዋቾች መቸኮላቸውን ትተው እዚህ ትልቅ እና አንጋፋ ክለብ ለመጫወት ትዕግስት ቢያደርጉ መልካም ነው ።


አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ ላይ ደጋፊው እምነት የለውም፡፡ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሞውን እያሰማ ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ ረገድ የክለቡ አቋም ምንድነው?

አዎ እሰማለው፡፡ ቅድም አጀማመሬ ላይ እንደነገርኩሁ ነው፤ ሁሉንም ነገር በሚገባ እየመረመርን እና እየፈተሸን ነው። ማንም የሚድን ሰው የለም ።


ስለዚህ በቅርቡ የአሰልጣኝ ለውጥ ይኖራል ማለት ነው ?

መልሴ ይኸው ነው ። የሚድን ሰው የለም ።


ሌሎች የሴቶች ቡድን ክለቦች ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀው ዝግጅት ጀምረዋል፡፡ እናንተ ጋር ግን እስካሁን ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም፡፡ የሴት ቡድናችሁን አፈረሳችሁት እንዴ?

እኛ አሁን ሙሉ ትኩረታችን ያደረግነው ዋናው ቡድን እና ታዳጊዎቹ ላይ ነው። የሴቶቹም ቡድን የሚናቅ ነገር የለውም፡፡ ግን የእኛ ክፍያ አነስተኛ ነው። በዚህም ምክንያት ሴቶቹ እየሸሹ ወደ ሌላ ክለቦች እየሄዱ ነው ያሉት። በአሁኑ ሰዓት በሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍሉ ክለቦች አሉ፤ አንዳንዶቹ የወንድ ቡድን ስሌሌላቸው ሙሉ በጀቱን ወደ ሴቶቹ እያዞሩ ከፍተኛ ብር እያወጡ ነው። እኛ ደግሞ ብዙ ኃላፊነት እና ስራዎች አሉብን፡፡ ወጣቶች አካዳሚን ዘንድሮ እናንቀሳቅሳለን፣ በአካዳሚውም ወደፊት ሴቶች እንዲገቡ እናስባለን፡፡ አሁን የወንዶቹን እንጀምረው እንጂ ወደፊት ሴቶች እንዲገቡ ሀሳብ አለን፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጊዮርጊስን ብለው በፍቅር የሚጫወቱ ካሉ ይምጡ እንጂ አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ ተወዳድረን የሴቶች ቡድን ይኖረናል የሚል ተስፋ የለኝም።


ቅዱስ ጊዮርጊስን ለረጅም ዓመት ያገለገሉ ተጫዋቾች ጋር ዘንድሮ ተለያይቷል። ተጫዋቾቹንም በክብር እንደሚሸኝ ሰምተናል፤ ይህ የክብር ሽኝት መቼ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል?

በእቅድ ደረጃ ይዘናል፤ እናደርጋለን፡፡ አሁን መጀመርያ ቅድሚያ የምንሰጠው ለክለቡ ነው። ክለቡን የት ደረጃ እናደርሳለን የሚለው ነው ቅድሚያ የምንሰጠው። እነዛ ባለውለታዎች ናቸው፤ ተከብረው እንዲሄዱ ወስነናል፡፡ ቀኑንም እንጠብቃለን። የሚቀጥለው ሳምንት ሊሆን ይችላል፤ የዛሬ ሦስት ወርም ሊሆን ይችላል። ግን ጊዜውን ጠብቀን የሚገባውን የክብር ሽኝት እናደርጋለን።


የክለባችሁ አመራር አዲስ ከተመረጠው አመራር ጋር ያለው መግባባት እንዴት ነው? በውሳኔዎቹ ቅሬታ እንዳለ  ይነገራል። በቀጣይ ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ ተቀራርቦ ለመስራትስ ክለቡ ምን አስቧል  ?

በመጀመርያ ሁሉም ክለቦች መከበር አለባቸው። አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ ማድረግ አያስፈልግም። ለሁሉም ክለብ እኩል ግምት መሰጠት አለበት። እኩል የሆነ የፍትህ አሰጣጥ ውሳኔ መኖርም አለበት ብዬ አስባለሁ። ይህ ከሆነ የሚያጋጨን ነገር አይኖርም ። አዲሱ ፌዴሬሽን በትክክል እስከሰሩ ድረስ አብረን እንጓዛለን፤ ካልሰሩ ደግሞ ያው ሁልጊዜ እንደሚደረገው ግጭቱ እየሰፋ ከሄደ ደግሞ እየተናቆሩ መሄድ ይጀመራል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለደጋፊያችን እና ለስፖርቱ ቤተሰብ አይጠቅምም ። ደጋፊዎቻችን በየክልል ሜዳዎች በፀጥታ አካላት መደደብደብ የለባቸውም፤ የሚገባቸውን ክብር ማግኘት አለባቸው። አምና የተመለከትናቸው ለክለባችን ክብር የማይመጥኑ ብዙ አስነዋሪ ድርጊቶች ተፈፅመው አልፈዋል። ይሄ ዘንድሮ በምንም መንገድ መደገም የለበትም ። ፌዴሬሽኑ ውድድሩ ከመጀመሩ እና ችግሮቹ ከመፈጠራቸው አስቀድሞ ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን። አዲሱ አመራርም ይሄን ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ዘንድሮም ብዙ ለውጥ ይኖረዋል ብዬ አላስብም ። ችግር ሲመጣ ብቻ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ጊዜያችንን ስንፈጅ እንከርማለን።


የክለቡ የዘንድሮ ዕቅድ ምድነው ?

አሁን ትኩረታችን እየተንከባለሉ የመጡ ክለቡን ችግር ውስጥ ሲከቱ የነበሩ ችግሮችን እየፈተሽን ማስተካከል ላይ ነው።  ሙሉ ትኩረታችን ደጋፊውም የሚፈልገው ጥሩ እና ውጤታማ ቡድን መስራት ነው። ጥሩ አሰልጣኝ እንዲኖረን በጣም እንፈልጋለን፤ ይሄን ማስተካከል አለብን ። እንደምትመለከተው እኔም እዚህ ቢሾፍቱ አካዳሚ ጊዜዬን ፈጅቼ እዚህ ልምምድ ላይ፣ የተጫዋች ምርጫ ላይ የምገኘው እንደከዚህ ቀደሙ ስህተቶች እንዳይደገሙ እና ደጋፊው የሚሰማው ስሜት ስለሚሰማኝ ይህን ለማስተካከል ነው። ስለዚህ በ2010 ያጣናቸውን ነገሮች በሙሉ 2011 ላይ ለማሳካት ጠንካራ ስራ ለመስራት አቅደን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ቅዱስ ጊዮርጊስ የፍቅር ቤት ነው፤ ተጫዋቾቹም ደጋፊዎቹም ክለቡን በፍቅር የሚወዱ ናቸው። የክለቡ አመራሮችም ስፖርቱን የሚያውቁ እና የሚወዱ ናቸው። በፍቅር ሆነን ይህን የምንወደውን ክለብ ታላቅ እናደርገዋለን።