ወልዋሎ ጊኒያዊ ግብ ጠባቂ አስፈረመ

በዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች ያስፈረሙት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ባለፈው ወር በቃል ደረጃ የተስማሙት እና በግል ጉዳዮች ምክንያት ሳይሳካ የቆየው የአብዱልአዚዝ ኬይታን ዝውውር ማጠናቀቃቸው ታውቋል፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የውስጥ ሃገር ግብ ጠባቂዎች ከሚጠቀሙት ጥቂት ክለቦች መካከል የነበሩት ቢጫ ለባሾቹ የቀድሞ የቢልድ ኮን ግብ ጠባቂ አብዱልዓዚዝ ኬይታን ማስፈረማቸው ተከትሎ የውጭ ሃገር ግብ ጠባቂዎች ከሚጠቀሙት ቡድኖች ተርታ ተቀላቅለዋል። ወልዋሎዎች በዚህ ክረምት ብዙ የግብ ጠባቂ አማራጮችን በመመልከት ከዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ እና ከደደቢት የለቀቀው ክሌመንት አማራህ ጋር ድርድር አድርገው የነበረ ቢሆንም ሳያስፈርሙ ቀርተዋል፡፡

አብዱልአዚዝ ባለፈው ዓመት በዛምቢያው ክለብ ቢልድ ኮን የተጫወተ ሲሆን ከዛ ቀደም በሀገሩ ክለቦች ካሉም ስታርስ እና ባራካ ክለቦች አሳልፏል፡፡ ከሀገሩ ጊኒ ጋር በ2012 የአፍሪካ ዋንጫ እና የ2016 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ተሳትፎን ጨምሮ ለ22 ጊዜ መጫወት ችሏል፡፡