ደቡብ ፖሊስ በረከት ይስሀቅን አስፈረመ 

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከረጅም ዓመታት በኃላ መልሶ የቀጠረው ደቡብ ፖሊስ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ ካደገ ማግስት ጀምሮ እያስፈረመ ይገኛል። አሁን ደግሞ የፊት መስመር ተሰላፊ የሆነውን በረከት ይስሀቅን በአንድ አመት የውል ስምምነት ወደ ክለቡ ቀላቅሎታል።

በ2001 ከሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን ተገኝቶ በዋናው ቡድን መጫወት ከቻለ በኃላ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ደደቢት እና ድሬዳዋ ካሳለፈ በኋላ ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ቢያመራም ስኬታማ ካልሆነ ግማሽ ዓመት በኋላ በድጋሚ ወደ ድሬዳዋ ተመልሶ ዓመቱን አጠናቋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ በሀዋሳ እና በድሬዳዋ አብሮት ከሰራው አሰልጣኝ ዘላለም ጋር ለሶስተኛ ጊዜ የሚገናኝ ይሆናል፡፡

በአጥቂ ስፍራ ላይ ፃዲቅ ሴቾ እና ካርሎስ ዳምጠውን አስፈርሞ የነበረው ደቡብ ፖሊስ አሰልጣኙ ማሳመን አልቻሉም በሚል ሲያሰናብት በቀጣይ በሙከራ ያሳለፉ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተጫዋቾችን ዝውውር እንደሚያጠናቅቅ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።